ነገ በሚደረገው ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ፋሲል ከነማ በወቅቱ ከቱኒዚያው ሴፋክሲያን ጋር በነበረበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ከ2ኛው ሳምንት በይደር የተያዘው ይህ ጨዋታ ነገ በድሬዳዋ 10:00 ላይ ይከናወናል።
መርሐ ግብሩ ለወላይታ ድቻ በጥሩ ጊዜ የመጣ አይመስልም። እስካሁን ሁለት ድሎችን ያሳኩት ድቻዎች ከተከታታይ ውጤት ማጣት በኋላ አዳማ ከተማን 2-1 መርታት ቢችሉም በቀጣይነት ከአርባምንጭ ከተማ ያለግብ ተለያይተው እና በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 ተሸንፈው ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። በተመሳሳይ በውጤት ማጣት ውስጥ የከረመው ፋሲል ከነማ ደግሞ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሲዳማ ቡናን መርታት የቻለባቸውን ውጤቶች አስመዝግቦ ተስተካካይ ጨዋታውን ያደርጋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በኋላ ካለባቸው የስብስብ ጥልቀት ችግር አንፃር የሚችሉትን ማድረግ ቢችሉም ከሽንፈት አለማምለጣቸውን ገልፀው ነበር። የነገው ተጋጣሚያቸውም በተመሳሳይ የቡድን ስብስብ ጥራት ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ከመሆኑ አንፃር ይህ አስተያየታቸው ነገም ከበድ ያለ ፈተና እንደሚገጥማቸው እንደሚያስቡ ፍንጭ ይሰጣል። በመሆኑም ወላይታ ድቻ የጨዋታውን ክብደት የሚመጥን ጥልቅ መከላከል ላይ ያተኮረ አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል። ነገር ግን ቡድኑ ተፈላጊውን ውጤት ይዞ ለመውጣት የቀደመ የመከላከል ጥንካሬውን ከመተግበር ባለፈ ይበልጥ የተዳከመውን በፈጣን ጥቃት እና በቀጥተኛ ኳሶች አደጋ የመጣል መንገዱን መልሶ ማግኘት ይጠበቅበታል።
የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ለገጣፎ ለገዳዲን ሲረቱ ቡድናቸው ላይ ያለውን ጫና የሚቀንስ ውጤት ስለማስመዝገባቸው ተናግረው ነበር። ይሄ ሀሳብ በሲዳማ ቡናው ጨዋታም ተንፀባርቋል። 4-2 በተፈፀመው ጨዋታ እንደቡድን ብቻ ሳይሆን በግልም አቋማቸው ወርዶ የነበሩ ተጫዋቾች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ መታየቱ ፋሲል ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክቶ ወገብ ላይ ከሆነው ደረጃው ወደ 4ኛነት ከፍ ለማለት ሊረዳው እንደሚችል ይገመታል። በተለይም በቀደመ ከፍ ያለ የማጥቃት ጫና በመፍጠር አቅሙ ላይ ሆኖ የታየው የቡድኑ የቀኝ ወገን ነገ ክፍተት ላለመስጠት በጥንቃቄ ሊቀርብ ከሚችለው የወላይታ ድቻ የመከላከል መዋቅር ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል።
ወላይታ ድቻ በጉዳት ምክንያት ከማያገኛቸው ተጫዋቾች መካከል መሳይ ኒኮል እና እንድሪስ ሰዒድ ወደ መደበኛ ልምምድ ለመመለስ የተቃረቡ ሲሆን ዮናታን ኤልያስ እና አንተነህ ጉግሳ ግን አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ። በፋሲል ከነማ በኩል በቡድኑ ውስጥ ከሌለው ሀብታሙ ተከስተ በተጨማሪ አስቻለው ታመነ በጉዳት ለጨዋታው የማይደርስ ሲሆን በዛብህ መለዮ ዛሬ ልምምድ ቢሰራም የመሰለፉ በጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ አስር ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ፋሲል ከነማ ስድስት ወላይታ ድቻ ደግሞ ሦስት ጊዜ አሸንፈው አንዴ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ 14 የጦና ንቦቹ ደግሞ 10 ጎሎችን አስመዝግበዋል።
ጨዋታውን ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ፣ ፍሬዝጊ ተስፋዬ እና ትንሳኤ ፈለቀ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ገመቹ ኤዳኦ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።