የአስራ አንደኛ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለትን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አርባምንጭ ከተማ
የዕለቱ የመጀመሪያ መርሃሐግብር የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድላቸውን የሚፈልጉትን ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ ድላቸውን ካሳኩት አርባምንጭ ከተማዎች ጋር ያገናኛል።
በጊዜያዊ አሰልጣኛቸው ገዛኸኝ ከተማ እየተመሩ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች ማግስት ባሳኩት አንድ ነጥብ ታግዘው በድምሩ በስድስት ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ከሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በአንድ ነጥብ ከፍ ብለው 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከአሰልጣኝ ለውጥ ማግስት ወደ ውጤታማነት ለመመለስ እየጣሩ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የውድድር ዘመናቸውን ወደ መስመር የሚመለስን ድል እያሰሱ ይገኛሉ። አቻ በተለያዩበት የመጨረሻ ጨዋታቸው በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ሜዳ ላይ ያሳዩት ጥቅል እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ የነበረ ሲሆን በተለይ በጨዋታው በመከላከሉ ቡድኑ የነበረው አፈፃፀም ጥሩ የሚባል ነበር። ከረጅሙ የሊጉ ጉዞ ሲሶው ያህል እስካሁን የተካሄደ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ውጥን ለማሳካት ነጥቦችን በጊዜ መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኮቹ ዘሪሁን ታደለ እና አላዛር ሽመልስ ከጉዳታቸው ካለማገገማቸው በተጨማሪ አጥቂው ልደቱ ለማም በልምምድ ላይ ቀለል ያለ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን ለነገው ጨዋታ መድረሱ እርግጥ አልሆነም።
በ3ኛ የጨዋታ ሳምንት ድል ካስመዘገቡ በኋላ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድላቸውን ፍለጋ አምስት ጨዋታዎችን ለመጠበቅ ቢገደዱም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ግን ዳግም ከድል የታረቁት አዞዎቹ በ10 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በኋላ የሦስት ተከላካዮች ወደ መጫወት የመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ይህ አደራደር የተመቻቸው ይመስላሉ። በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ጥሩ የነበረው ቡድኑ አዳማ ከተማን በረቱበት ጨዋታ በርከት ያሉ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ቢገደዱም ጨዋታውን የተቆጣጠሩበት መንገድ አስደናቂ ነበር። አዳማን በመርታት ወደ ድል የተመለሱት አርባምንጭ ከተማዎች ነጥባቸውን ሆነ በሰንጠረዡ ያላቸውን ደረጃ ለማሻሻል ይህን ድል እንደ መነሻ በመጠቀም አሸናፊነታቸውን ለማስቀጠል በነገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአርባምንጩ አጥቂ ተመስገን ደረሰ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ እንቅስቃሴ ሲመለስ በቡድኑ ውስጥ የተሰማ ሌላ የጉዳት ዜና የለም።
ከ2004 ጀምሮ ከፕሪምየር ሊግ እስከወረዱበት 2010 ድረስ ሁለቱ ቡድኖች ለ14 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን ኤሌክትሪክ 6 ፣ አርባምንጭ 4 አሸንፈዋል። 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 18 ፣ አርባምንጭ 13 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
10 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገውን ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ገመቹ ኤዳሆ ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ዳዊት ገብሬ ረዳቶች ፣ አባይነህ ሙላት ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድቧል፡፡
ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል
የምሽቱ መርሐግብር ወጥ ብቃትን ለማሳየት የተቸገሩትን ሀዋሳ ከተማዎችን ከመቻል ጋር ያገናኛል።
ከተከታታይ ድሎች ማግስት በመጨረሻ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ የሰበሰቡት ሀዋሳ ከተማዎች በ15 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ወጥ የሆነ ብቃትን ለማሳየት የተቸገሩት ሀዋሳ ከተማዎች ለጥንቃቄ ትኩረት በሚሰጥ አቀራረብ መጫወት ምርጫቸውን ቢያደርጉም ከሰሞኑ የሚያገኟቸውን ጥቂት የማጥቃት አጋጣሚዎችን ይበልጥ እንዲጠቀሙ የሚያደርጓቸውን ተጫዋቾች በጉዳት ማጣታቸውን ተከትሎ ማጥቃታቸው ክፉኛ ተቀዛቅዟል። በሊጉ ካስተናገዱት ግብ ዕኩል ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ቡድኑ በቀራረብ ረገድ አዎንታዊነት ጨምረው መጫወት የግድ የሚላቸው ይመስላል። ሌላው ከሀዋሳ ጋር የሚነሳው ጉዳይ ቡድኑ በመጨረሻ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት የቀይ ካርድ የመመልከታቸው ጉዳይ ነው። ሀዋሳዎች ጨዋታዎችን በሙሉ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጨረስ መቸገራቸው ውጤቶችን ለመቀልበስ ሆነ ይዞ ለመውጣት እንዲቸገሩ እያደረገ ይገኛል።
በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ብርሀኑ አሻሞ ከቅጣት ሲመለስ በዘርዓይ ሙሉ ስብስብ ውስጥ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ወሳኝ ሚናን እየተወጡ የነበሩት አዲሱ አቱላ እና ሙጂብ ቃሲም አሁንም በጉዳት አይኖሩም፡፡
በውጤት አልባ ጉዞ ውስጥ የሚገኙት እና አሁንም በከፍተኛ ጫና ውስጥ እየተጫወቱ የሚገኙት መቻሎች በ9 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በ4ኛ የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን ከረቱ ወዲህ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ጊዜ ሲሸነፉ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። እንደ ቡድን ብዙ የተጠበቀበት ስብስቡ ድልን ከመራቡ ባለፈ በሜዳ ላይ የሚያሳዩት እንቅስቃሴም ፍፁም ደካማ የመሆኑ ጉዳይ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። በተለይ ከወገብ በላይ ጥራታቸው በንፅፅር የላቁ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ብቻ ግቦችን ማስቆጠሩ ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ይበልጥ የሚያስጨንቅ እውነታ ነው።
በአሁንም ጨዋታ መቻሎች የተሾመ በላቸውን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን የተቀሩት ተጫዋቾች ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 30 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች 14 እንዲሁም መቻሎች 7 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን የተቀሩት 9 ጨዋታዎች ግን በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።
የምሽቱን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ፣ ፍሬዝጊ ተስፋዬ እና ክንፈ ይልማ በረዳትነት ፣ ብርሀኑ መኩሪያ በአራተኛ ዳኝነቴ ለጨዋታው ተመድቧል፡፡