የአሠልጣኞች አስተያየት | መቻል 1-1 ወልቂጤ ከተማ

“ጫና ውስጥ ነኝ ፤ ከዚህ ጫና ለመውጣት ግን የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው” ፋሲል ተካልኝ

“ተጫዋች ሜዳ ላይ እንደሚሳሳተው ሁሉ ዳኞችም ሊሳሳቱ ይችላሉና እንደሰው ወስደንላቸው እንተወው” ገብረክርስቶስ ቢራራ

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – መቻል

ስላደረጉት እንቅስቃሴ….

በመጀመሪያው አጋማሽ በጠበኩት መልኩ አይደለም የተጫወትነው ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ለማሻሻል ሞክረናል። ጎሉ የገባብን የእኛ ተከላካዮች በቆሙበት ነው ፤ በትኩረት ማነስ የተቆጠረብን። ግን ከእዛ በኋላ ጨዋታውን ለመገልበጥ ሞክረናል። ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘታችን በቂ ነው ባይባልም ከመመራት ተነስተን አንድ ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ነው።

ከሀዋሳው ጨዋታ ወረድ ያለ አቋም ስለማሳየታቸው…

በየጨዋታው ሦስት ነጥብ እንፈልጋለን። ይህንን ተከትሎ ከአደገኛው ቀጠና እስክንወጣ እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት ማሸነፍ እንሞክራለን። ጫና ውስጥ ነኝ ፤ ከዚህ ጫና ለመውጣት ግን የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ነው።

በጨዋታው ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ስላለመፍጠራቸው…

ወልቂጤ አራት የማይነቀሉ ተከላካዮችን እየተጠቀመ ነበር። እነርሱን ለመስበር ሞክረናል። አጋጣሚዎችንም አግኝተን ነበር ፤ እነርሱን ወደ ውጤት መቀየር ካልሆነ በስተቀር። ሳጥን ውስጥም ከውሳኔ ስህተት የመከኑ አጋጣሚዎችንም አጥተናል።

ስለአቻው ውጤት…

ከመመራታችን አንፃር አንድ ነጥብ ማግኘታችን መጥፎ አይደለም።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በፈለግነው መንገድ ሄዷል። በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረብን የፍፁም ቅጣት ምት ግን አቻ ወጥተናል ፤ ይህንንም እንቀበላለን።

ስለተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት ምት…

እኔ ሩቅ ነኝ። ፊልሙን ባይ መልስ ልሰጥ እችላለው። እኔ በዳኝነት ጉዳይ ብዙ ጊዜ መልስ መስጠት አልወድም። እሱ የራሱን ሥራ ይሰራል ፤ እኔም የራሴን ነው የምሰራው። ምክንያቱም ወደ ሰው ከጠቆምኩም የራሴን ስህተት ማየት ይከብደኛል። ስለዚህ የራሳችንን ድክመት ለማረም እንጥራለን።

በመጨረሻ ደቂቃ ስለሚቆጠርባቸው ጎሎች…

የተቆጠሩብን የመጨረሻ ደቂቃዎች ጎሎች ፊልማቸው ቢታይ ተገቢ ናቸው ወይስ አይደለም የሚለውን መለየት ይቻላል። በዳኝነት ጉዳይ አስተያየት መስጠት ስለማይቻል እንተወው ብዬ እንጂ ከመጀመሪያ ጀምሮ ዝርዝሩን ልናገር እችላለው። ይህ ይቅርና እኛ ወደራሳችን ስህተቶች እናተኩር። ተጫዋች ሜዳ ላይ እንደሚሳሳተው ሁሉ ዳኞችም ሊሳሳቱ ይችላሉና እንደሰው ወስደንላቸው እንተወው።