ነገ በሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
የዕለቱ የመክፈቻ መርሃግብር በሜዳቸው አልቀመስ ያሉትን ድሬዳዋ ከተማዎችን ከወላይታ ድቻ ያገናኛል።
በሜዳቸው አውንታዊ ነጥቦችን እየሰበሰቡ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ላይ በ18 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከውጤቶች ባለፈ ግን ቡድኑ ጨዋታዎችን የሚጀምርበት መንገድ ጥያቄ የሚነሳበት ነው። ሆኖም ቀድሞ ግብ ማስተናገድ የተደጋገመበት ቡድኑ ጨዋታውን በማሳደድ ቢያደርግም ወደ ጨዋታ ለመመለስ እምብዛም ሲቸገር አናስተውልም። አሁንም በቀጥተኛ አጨዋወት በተለይም የቢኒያም ጌታቸውን ፍጥነት የሚተማመነው ድሬዳዋ በመጨረሻው ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ ለቡድኑ የራስ መተማመን የሚጨምር ይመስላል።
በ12 ነጥቦች በሰንጠረዡ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ፋሲልን በረቱበት የመጨረሻ ጨዋታቸው የቡድኑ የአጨዋወት መሰረቶችን የሆኑትን ቢኒያም ገነቱ ፣ ደጉ ደበበ እና ንጋቱ ገብረስላሴን ዳግም ማግኘቱ ቡድኑ ወደ ቀደመ ማንነቱ የመለሰው ይመስላል። ይህም በተለይ ድቻዎች መከላከሉ እጅግ ተሻሽለው እንዲቀርቡ ከማስቻል ባለፈ በተለይ በሚታወቁበት ፈጣን ሽግግር ይበልጥ ስልነትን አላብሷቸው አስተውለናል።
በድሬዳዋ ከተማ ዳንኤል ተሾመ ፣ ያሬድ ታደሰ ፣ አቤል ከበደ ፣ አቤል አሰበ በጉዳት ዮሴፍ ዮሐንስ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ልምምድ እየሰራ ባለመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። እንየው ካሳሀን ደግሞ ከቅጣት ይመለሳል።
በወላይታ ድቻዎች በኩል መጠነኛ ጉዳት ያስተናገዱት ሀብታሙ ንጉሴ እና ሳሙኤል ተስፋዬ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ከመሆኑ ባለፈ የተቀረው ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
ሁለቱን ቡድኖች እስካሁን ካገናኟቸው 12 ጨዋታዎች ውስጥ አራቱ ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ 13 ግቦች ያስቆጠሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ሰባት እንዲሁም 7 ግቦች ያስቆጠሩት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አንድ ድል አስመዝግበዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት ጨዋታውን ሲመራው ፣ በቅርቡ ከከፍተኛ ሊግ ያደጉት ዘመኑ ሲሳየነው እና ሰብስቤ ጥላሁን በረዳት ዳኝነት በተመሳሳይ የማደግ ዕድልን ያገኙት መለሰ ንጉሴ በአራተኛ ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል። በዚህም ከበአምላክ ውጪ ሦስቱም ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታን የሚመሩ ይሆናል፡፡
ሲዳማ ቡና ከ ባህር ዳር ከተማ
የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በሊጉ ፍፁም ደካማ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙትን ሲዳማ ቡናዎች ከወቅቱ የሊጉ ጠንካራው ቡድን ባህር ዳር ከተማ ያገናኛል።
በ10 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች አሁንም በሁሉም ዲፓርትመንቶች ወጥ ብቃት ማሳየት ተስኗቸዋል። የውድድር ዘመኑን ስድስተኛ ሽንፈታቸውን ባስተናገዱበት የፋሲሉ ጨዋታም በተለይ የኋላ መስመራቸው ተፍረክርኮ ተስተውሏል። ነገር ግን ቡድን ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ ለቀናት እረፍት አድርጎ የመመለሱ ጉዳይ ክፍተቶቹን ለማረም ይረዳዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በነገው ጨዋታ ሰልሀዲን ሰይድ እና አማኑኤል እንዳለ በጉዳት እንዲሁም የግብ ጠባቂያቸው መክብብ ደገፉን ግልጋሎት ደግሞ በቅጣት አያገኙም።
በሰንጠረዡ አናት ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ አንሶ በ21 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታዎቸው ነጥብ ከመጋራታቸው አስቀድሞ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ያገኟቸውን የግብ እድሎች በግለሰባዊ ስህተቶች መጠቀም ሳይችሉ ቢቀሩም ቡድኑ በወቅታዊ ብቃት በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ የሊጉ ምርጡ ቡድን ስለመሆኑ መናገር ይቻላል።
ባህር ዳር ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ፋሲል አስማማውን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀምም።
ተጋጣሚዎቹ እስካሁን ስድስት የሊግ ጨዋታዎችን እርስ በእርስ አድርገዋል። ባህር ዳር ከተማ ሦስት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ዘጠኝ ሲዳማ ቡና ደግሞ ስምንት ግቦች አስመዝግበዋል።
በጨዋታው ባህሩ ተካ በመሀል ዳኝነት ፣ ባደታ ገብሬ እና የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚመራው ደስታ ጉራቻ በረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።