በነገው ዕለት የሚደረገውን ብቸኛ መርሃግብር የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ይቀርባሉ።
ሃዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ መዘዋወሩን ተከትሎ ነገ የሚደረገውን ብቸኛ መርሃግብር ሃዋሳ ከተማን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኛል።
ከመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን የጣሉት ሃዋሳ ከተማዎች ከአስራ አንድ ጨዋታዎች በኃላ በአስራ አምስት ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከዚህ ቀደም እንደገለፁት በተነሳሽነት ረገድ ጉድለቶች እየተስተዋሉበት የሚገኘው ቡድኑ በተጋጣሚዎቹ ከኳስ ጋር ሆነ ከኳስ ውጭ ለሚወሰድበት ብልጫ ምላሽ ለመስጠት እየተቸገረ ይገኛል። ይህ የተነሳሽነት ጉድለት የቡድኑ መገለጫ የሆኑትን የመከላከከል ጥንካሬ እና ሆነ ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች ፍፁም እንዲዳከሙ አድርጓቸዋል።
በነገው ጨዋታ ሃዋሳዎች ጉዳት ላይ የነበረውን አማካያቸው አዲሱ አቱላን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ወሳኙ አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም ግን አሁንም በጉዳት አይኖርም፡፡
ከተከታታይ ሽንፈቶች ማግስት በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ያሳኩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች አሁንም ከሊጉ ግርጌ በሁለት ነጥብ ከፍ ብለው በሰባት ነጥብ አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የተቸገረው ቡድኑ ከአሰልጣኝ ለውጥ ማግስት ከጨዋታ ጨዋታ መጠነኛ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል።በመጨረሻው የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በተለይ ቡድን በብዙ መንገድ የተሻለ ጊዜ አሳልፈዋል ፤ በጨዋታው ከመመራት ተነስተው ጨዋታውን ለመገልበጥ ጥረት ያደረጉበት መንገድ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ያደረጓቸው ለውጦች ቡድኑ ላይ የፈጠሯቸው ለውጦች በጨዋታው መልክ ላይ የነበራቸው አውንታዊ ተፅዕኖ ስለቡድኑ መሻሻል አይነተኛ ማሳያ ናቸው።
በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል የመስመር ተጫዋቹ አላዛር ሽመልስ ከጉዳቱ ቢያገግምም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን አጥቂው ልደቱ ለማም በጉዳት የነገው ጨዋታው ያልፈዋል።
10 ሰዓት ሲል የሚጀምረውን የዕለቱን ብቸኛ መርሃግብር ተፈሪ አለባቸው በመሀል ዳኝነት ፣ አያሌው ማንደፍሮ እና ኤልያስ መኮንን በረዳትነት እንዲሁም ዳንኤል ግርማይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።