ከቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸው ውል የተቋረጠባቸው አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ጉዳያቸውን ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ እንደወሰዱ ታውቋል።
ባሳለፍነው ክረምት አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌን በመተካት የኢትዮጵያ ቡና አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ተመስገን ዳና ከውጤት መጥፋት ጋር በተገናኘ ከክለቡ ጋር ያላቸው ውል እንዲቋረጥ እንደተደረገ ይታወቃል።
ድረ-ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ አሁን የደረሳትን መረጃ ተመርኩዛ የአሠልጣኙን ጉዳይ ከያዙት የህግ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው እንዳረጋገጠችው ከሆነ አሠልጣኝ ተመስገን ዳና “ያለ አግባብ ህጋዊ ውሌ ተቋርጧል” ብለው ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፍትህ አካል የክስ ደብዳቤ አስገብተዋል።
አሠልጣኙ ባስገቡት የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ ወርሀዊ ደመወዛቸውን እስከ ጥቅምት ወር ድረስ መውሰዳቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ቡና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ውሉን በማፍረሱ እስከ ውላቸው ማብቂያ የቀሪ 19 ወራት ደመወዝ እንዲከፈላቸው እና መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።