የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ወደ መሪነት ከፍ ሲል ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የስድስተኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ሦስት ነጥብ ሸምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ የሳምንቱ ቀዳሚው ጨዋታ ነበር፡፡ 04፡00 ሲል በኢንተርናሽናል ዳኛ ፀኃይነሽ አበበ በተመራው በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተመጣጣኝነት ያለው ፉክክር የተመለከትን ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትሩ አስተውለናል፡፡ መሀል ሜዳ ላይ ሰናይት እና ብርቱካን የጨዋታው መነሻ በማድረግ ለመጫወት ሲዳዱ የታዩት ንግድ ባንኮች 30ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የአዲስ አበባ የግብ አካባቢ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት እፀገነት ብዙነህ አክርራ የላከቻት ኳስ የግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ ስህተት ታክሎበት ቡድኑ መሪ ሆኗል፡፡ የንግድ ባንክን የመከላከል መንገድ አስከፍቶ ጎልን ለማስቆጠር የኃይል ሚዛናቸውን ወደ ማጥቃቱ ያሸጋገሩት አዲስ አበባዎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በአስራት ዓለሙ ጎል አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሎዛ አበራ ንግድ ባንክን ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡

IMG_20221214_193618_390

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ አዲስ አበባዎች ከማጥቃት ይልቅ የኋላ መስመራቸውን በማስጠበቁ ሲቀጥሉ ንግድ ባንኮች በአንፃሩ በይበልጥ ወደ ማጥቃት አተኩረው በመግባት በፈጠሩት ጫና ግቦችን አስቆጥረዋል፡፡ በነበራቸውም ብልጫ ሎዛ አበራ 52ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ማራኪ ጎል ከርቀት ስታስቆጥር ተቀይራ የገባችው መሳይ ተመስገን መደበኛው ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል ሲቀረው አራተኛ ጎል አክላ ጨዋታው 4-1 በሆነ የንግድ ባንክ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የንግድ ባንኳ እፀገነት ብዙነህ የጨዋታው ድንቅ በመባል ተሸልማለች፡፡

በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መካከል ሁለተኛው የሳምንቱ ጨዋታ ቀጥሎ ተደርጓል፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስት የተመጣጠነ የአጨዋወት ሂደትን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያስተዋልን ቢሆንም ከሌላ ጊዜ በተሻለ ለመፎካከር ይጥሩ የነበሩት ንፋስ ስልኮች የኋላ መስመራቸው ላይ በሚሰሩ ስህተቶች ጎልን ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ ከመስመር መነሻቸው ካደረጉ ኳሶች ጥቃት ይሰነዝሩ የነበሩት የአሰልጣኝ መሠረት ማኔዎቹ ኤሌክትሪኮች በኩል 38ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው አስደናቂ የነበረችው ሽታዬ ሲሳይ ከቀኝ ወደ ጎል የላከቻትን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው ምንትዋብ ዮሐንስ ወደ ጎልነት ለውጣ ቡድኑን መሪ አድርጋለች፡፡

IMG_20221214_193617_976

ሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት ኃይል ብልጫ ለመውሰድ ሲቃጡ የታዩት ኤሌክትሪኮች በመስከረም ካንኮ ጎል የጎል መጠናቸውን አስፍተዋል፡፡ አጥቂዋ ሰላማዊት ጎሳዬ እንዲሁም ከህይወት ደንጊሶ የተሻማን የቅጣት ምት ኳስ መስከረም ካንኮ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛውን ጎል በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ጨዋታ በአራት ለምንም ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በተደጋጋሚ ልዩነት ስትፈጥር የታየችው ሽታዬ ሲሳይ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡

የቀኑ የመጨረሻ ጨዋታ በነበረው እና የሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ ከግብ ሙከራዎች ይልቅ አስደሳች ፉክክሮችን አስመልክቶናል። ጨዋታው ያለ ግብ ዘልቆ 77ኛው ደቂቃ ላይ የቦሌዋ ተከላካይ ሒሩት ተስፋዬ በዓይናለም ዓለማየሁ ላይ ባሳጥን ውስጥ የሰራቸውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ ከመረብ አሳርፋው ጨዋታው በእንስት ፈረሰኞቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የጎሉ ባለቤት የሆነችው እየሩስ ወንድሙ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተመርጣለች፡፡

IMG_20221214_193618_084