ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግቦች ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ተቆጥረዋል ፤ እኛም እነዚህን ግቦች መነሻ በማድረግ የተወሰኑ ሀሳቦችን ለማንሳት ወደናል።
ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በተደረገው የመጨረሻው 13ኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ሃያ ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ግቦቹ የተቆጠሩበትን ደቂቃዎች ከተመለከትን አንዳች የሚነግሩን ነገር አለ። አንድን የጨዋታ አጋማሽ በሦስት አስራ አምስት ደቂቃዎች ከፋፍለን ከተመለከትን ከተቆጠሩት ግቦች ውስጥ ስድስቱ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት እንዲሁም ተጨማሪ ስድስት ግቦች ደግሞ በአጋማሾቹ ባሉት የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃዎች የተመዘገቡ ናቸው። ይህም ማለት በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትነው አጠቃላይ የግብ መጠን ውስጥ 60% የሚሆኑት ግቦች የተቆጠሩት በጨዋታው የመጀመሪያ እና የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
ይህንን የጨዋታ ሳምንት ለአብነት አነሳን እንጂ አብዛኞቹ የጨዋታ ሳምንታት ላይ የምንመለከታቸው ቁጥሮች ከዚህ ብዙም የራቀ አለመሆኑ የሊጉ ክለቦች ሙሉ ዘጠና ደቂቃ በትኩረት ከመጫወት አንፃር ስላለባቸው ችግር በተለይ በጨዋታ መጀመሪያ እና መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ከትኩረት ማነስ ጋር ተያይዞ ስለሚሰሯቸው አደገኛ ስህተቶች እና ስለሚያስተናግዷቸው ግቦች ዓይነተኛ ምስል ይሰጠናል። በእግር ኳስ ውጤታማ ስለሆኑ ታላላቅ ቡድኖች ስናስብ ከጨዋታው ጅማሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ በትኩረት ስለመጫወታቸው ማንሳታችን አይቀርም። በአንፃሩ በእኛ ሀገር ደረጃ ከክለቦቻችንም በላይ በብሔራዊ ቡድኖቻችን ጭምር ትኩረት ማጣት ዋጋ ሲያስከፍለን እንደመኖሩ ይህንን ነጥብ እንደ አንድ የእግርኳሳችን ድክመት በትኩረት ማየት ይገባናል።
ውጤታማ ቡድን ለመሆን በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች(Phase of Play) በትኩረት መጫወትን የሚጠይቅ ቢሆንም በተለይ መከላከል (በክፍት ጨዋታም ሆነ ከቆሙ ኳሶች) ግን የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ፍላጎት የማምከን ሂደት እንደመሆኑ የላቀ የትኩረት ደረጃን የመፈለጉ ነገር አያጠራጥርም። ታድያ በዚህ ረገድ የሊጉ ተካፋይ ቡድኖች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታቸውን ዝግ ባለ መልኩ የመጀመራቸው እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተለይ ደግሞ የሚያስጠብቁት ውጤት ያላቸው ቡድኖች የሚከላከሉበት መንገድ ፍፁም በስህተቶች የተሞላ የመሆኑ ነገር አሳሳቢ ነው።
ሌላው መነሳት የሚገባው መሰረታዊው ጉዳይ የቡድኖች አደረጃጀት ጉዳይ ነው። እግርኳስ የቡድን ስፖርት እንደመሆኑ አስራ አንዱ ተጫዋቾችን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተደራጀ መዋቅር መኖሩ እጅግ ወሳኝ ነው። በዓለም ዓቀፍ እግርኳስ አሁን ላይ ቡድኖች በተለያዩ የጨዋታ ምዕራፎች ልምምድ ሜዳ ላይ እጅግ አድካሚ የሆኑ ተደጋጋሚ ስራዎችን በመስራት በጨዋታ ወቅት ከተጫዋቾች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም (Improvisation) ይልቅ በልምምድ ሜዳ ላይ በጥልቀት በተሰሩ ተጫዋቾች በደመነፍስ በሚያውቋቸው አስቀድመው የታቀዱ መንገዶች(Automatisms) መጫወት በጣም እየተለመደ መጥቷል። ከዚህ ዓለምዓቀፋዊ ተሞክሮ አንፃር የሀገራችን እግርኳስን ማነፃፃር በራሱ ኢፍትሃዊ ይመስላል ፤ የእኛ ቡድኖች አሁን ድረስ ከጥቂቶቹ ውጭ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ እንዲሁም በሽግግሮች እና በቆሙ ኳሶች ወቅት የሚያደርጉትን ስለማወቃቸው ፍፁም ያጠራጥራል።
አደረጃጀት መነሻው ግለሰቦች ሆኖ ግቡ ደግሞ ቡድን ነው። ቢሆንም በሀገራችን እግርኳስ ግን በዚህ ረገድ ብዙ ውስንነት አለ። ለዚህ ፅሁፍ እንዲሆነን በተለይ በመከላከል ወቅት ያለው የቡድኖች አደረጃጀት በጥቂት ማሳያዎች እንመልከት።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ለገጣፎ ለገዳዲን 4-0 በረታበት ጨዋታ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ያስቆጠራት ፈጣኗ ግብ ከመረብ ስትገናኝ የነበረው ሂደት ስለቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ድክመት ዓይነተኛ ማሳያ ነው። 28 ግቦችን በማስተናገድ የሊጉ እጅግ ደካማው የመከላከል መስመር ባለቤት የሆኑት ለገጣፎዎች የጨዋታ ማብሰሪያ ፊሽካ ከተነፋ ከዘጠኝ ሰከንድ በኋላ ግቧን ሲያስተናግዱ ገና ከጅምሩ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ተጫዋቾቻቸው የነበራቸው አቋቋም በራሱ ችግር የነበረበት ነበር።
ኳሱን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለማስጀመር ሲዘጋጁ በለገጣፎ ለገዳዲ ተጫዋቾች በኩል ግን ገና በአቋቋም ረገድ ዝግጁ አልነበሩም። ኳሷም ከተጀመረች በኋላም ፍሪምፖንግ ሜንሱ በአግድሞሽ በተጣለው ረጅም ኳስ ስድስት የሚጠጉ የለገጣፎ ተጫዋቾችን ከኋላ አራት ተከላካዮቻቸው መነጠል የቻለ ሲሆን የለገጣፎው የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው ኪሩቤል ወንድሙ መነሻ አቋቋሙ ትክክል ያልነበረ መሆኑን ተከትሎ ኳሱን ለመሻማት ሆነ ለማስጣል በሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳይገኝ ያደረገው ነበር። ኳሱን የተቀበለው አማኑኤል ገ/ሚካኤልም ኳሷን በግሩም አንድ ንክኪ ወደ ሳጥን ሲያሻማም ለገጣፎዎች ሳጥን ውስጥ ተጨማሪ አንድ ተጫዋች የነበራቸው ቢሆንም ተከላካዮች የነበራቸው ቦታ አያያዝ እና ኳሷን ለመከላከል የሄዱበት ርቀት ደካማ መሆኑን ተከትሎ ኳሷ በቀላሉ ልትቆጠር ችላለች።
ሌላኛው በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትናቸው ጨዋታዎች ፈጣኗን ግብ ያስመለከተን በነበረው ጨዋታ አዳማ ከተማ ድሬዳዋን ሲረታ ቢኒያም አይተን 35ኛ ሰከንድ ላይ ያስቆጠራትን ግብ እንዲሁ የሊጉ ቡድኖች ስላለባቸው የመከላከል ችግር ማሳያ ነው። ሄኖክ ሀሰን አዳማ ከተማዎች ኳሱን መልሰው ለማግኘት ጫና እያሳደሩበት ባለበት ሁኔታ ወደ ኋላ የመለሰለትን ኳስ የተቀበለው አማረ በቀለ ገና ከጅምሩ ኳሱን ሲቀበል የነበረው የሰውነት ሁኔታ (body positioning) እና ኳሱ ከተቀበለ በኋላ በጫና ውስጥ ቢሆን እንኳን በቀላሉ ኳሱን ማራቅ ቢችል አልያም ከመሀል ተከላካይ አጣማሪው እያሱ ወይንም የግራ መስመር ተከላካዩ ጋዲሳ መብራቴ ማቀበል ሲችል ኳሱን በማዘግየቱ ራሱን ጫና ውስጥ የከተተ ሲሆን በዚህም ቢኒያም አይተን ኳሱን ነጥቆ በቀላሉ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ሁለቱን ግቦች ከተቆጠሩበት ደቂቃ እና ግቦቹ ሲቆጠሩ ከነበሩ የትኩረትም ሆነ የአደረጃጀት ክፍተቶች አንፃር አነሳን እንጂ የሚሻሙ ኳሶችን በመከላከል ወቅት ኳስን እንጂ ተጋጣሚን ያለመቃኘት ፣ በአንድ ለአንድ ፍልሚያዎች ወቅት ለማሸነፍ ከፍ ያለ ፍላጎት አለማሳየት ፣ በመከላከል ወቅት ሚዛን ያለመጠበቅ እና ወደ ሳጥን ዘግይተው የሚደርሱ የተጋጣሚ ተጫዋቾችን መቆጣጠር አለመቻል የሊጉ ቡድኖች መሰረታዊ የመከላከል ችግሮች እንደሆኑ ቀጥለዋል። እነዚህ ጉዳዮች ግለሰባዊ በሚመስሉ ስህተቶች ይሸፈኑ እንጂ መሰረታዊ መነሻቸው መዋቅራዊ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ከዚህ ባለፈ ግን ግቦቹን ላስቆጠሩት ቡድኖች እውቅና መስጠት በእጅጉ ያስፈልጋል። በተለይም ቡድኖች የተጋጣሚን ደካማ ጎን አስቀድመው በማጥናት ይህን ለመጠቀም እያደረጉ ስለሚገኘው ዝግጅት የሚነግረን ነገር አለ። ይህም የቡድኖችን ደካማ ተጫዋቾች ሆነ ደካማ ወገን በመለየት እነዚያን ጉድለቶች የመጠቀም ፍላጎት ስለመኖሩ ያሳያል። በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊሷ ግብ ደግሞ ቡድኖች ጨዋታዎችን በመጀመር ሂደት ወቅት በጥቂት የተጠኑ የኳስ ንክኪዎች አደጋ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ስለመጀመራቸው የሚያሳይ ሲሆን ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተመሳሳይ ጨዋታን በማስጀመር ሂደት ከነበረ የቅብብል ሂድት ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘታቸው የሚዘነጋ አይደለም።
የእግር ኳሳችን የሜዳ ውስጥ ጉዳዮች ከችግሮች ጋር ተያይዘው የሚነሱ መሆናቸው እንዳለ ሆነ አብዛኞቹ በተለይም ከመከላከል ጋር የሚስተዋሉት መሠረታዊ ችግሮች በማጥቃት ጨዋታ ወቅት ባሉብን ድክመቶች የተሸፈኑ ይመስላል። በመሆኑም የሊጉን የፉክክር ጥራት ከማሳደግ አንፃር ቡድኖቻችን በመከላከሉ ረገድ ያለባቸውን የትኩረት እና የአደረጃጀት ችግሮች ለመቅረፍ ከወትሮው በተሻለ መስራት ይኖርባቸዋል።