የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን ያሰፋበትን ድል ሲያገኝ አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክም ድል አሳክተዋል።
4 ስዓት ላይ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አስገራሚ ተሳትፎን እያደረገ የዘለቀውን ልደታ ክፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ተጀምሯል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር ተመልክተናል። መሀል ሜዳ ላይ ያመዘኑ የኳስ ቅብብሎች በበዙበት በዚህኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች ሰናይት ቦጋለ እና እመቤት አዲሱ በሚፈጥሩት ስብጥር ለአጥቂዎቹ መዲና ፣ ሎዛ እና አረጋሽ በማድረስ ጎልን ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቢታዩም በቀላሉ በጊዜ የልደታን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ግን አልቻሉም። በአንፃሩ ከመሀል ሜዳ ወደ አጥቂ ክፍል በሚሻገሩ ኳሶች ጥቃቶችን በመፍጠር ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የአሰልጣኝ ፍቅሬ ቢሆነኙ ልደታ በእጅጉ ታትሯል ፣ ይሁን እንጂ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል በድንቅ አጨራረስ ጎል አስቆጥራ ንግድ ባንክን ቀዳማ አድርጋለች።
ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል ልደታ ክፍለ ከተማዎች ከመጀመሪያው አርባ አምስት መቀዛቀዝ መቻላቸው ለንግድ ባንክ የበላይ ሆኖ መገኘት ዕድልን የፈጠረ ሆኗል። 57ኛ ደቂቃ ላይ ጨዋታው ሲደርስም ተቀይራ የገባችው መሳይ ተመስገን ከማዕዘን መነሻን ያደረገ ኳስን ስታሻማ ብርቄ አማረ በግንባር ገጭታ ወደ ጎልነት ለውጣው የንግድ ባንክን የጎል መጠን ወደ ሁለት አሳድጋለች። የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ቁጥጥር በይበልጥ በማድረግ ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ሎዛ አበራ በአራት ደቂቃዎች ልዩነት አከታትላ ሁለት ድንቅ ጎሎችን አስቆጥራ ወደ 4ለ0 ቡድኗን ስታሸጋግር የሊጉን የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትም በ11 ጎሎች እንድትመራ አስችሏታል። ጨዋታውም በንግድ ባንክ 4ለ0 በሆነ ድል አድራጊነት ሲገባደድ ቡድኑም ሉጉን በነጥብ ልዩነት መሪነቱን እንዲያስቀጥል ሆኗል።
ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች አዲስ አበባ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ጨዋታ የቀኑ ሁለተኛ መርሀግብር ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስ ሙሉ በሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቀዳሚው አጋማሽ ያሳየን ቢሆንም ቡድኑ ረጅም ደቂቃን ኳስን ተቀባብለው የተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ መድረስ ቢችሉም በቀላሉ የሚያገኟቸውን ግልፅ ዕድሎች ከመረብ በማገናኘቱ ረገድ ግን ፍፁም ደካሞች ነበሩ። በተጋጣሚያቸው ተበልጠው በጨዋታው አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የሚያሳልፉት አዲስ አበባ ከተማዎች በአንድ አጋጣሚ 42ኛ ደቂቃ ላይ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በሄዱበት ወቅት ተከላካዮች በእጅ ኳስ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሰርካዲስ ጉታ ወደ ጎልነት ቀይራው ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች።
የተመጣጠነ ፉክክርን ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ 59ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል በእየሩስ ወንድሙ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሚረዳውን ጎል ከመረብ ቢያገናኙም 75ኛው ደቂቃ ላይ ቤቴልሄም መንተሎ በቀድሞው ክለቧ ላይ ጎል በማስቆጠሯ ጨዋታው በአዲስ አበባ 2-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የሆነው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክርን አስመልክቶን የተጠናቀቀ ነበር። በርካታ ተመልካቶች በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ተገኝተው በተመለከቱት በዚህ ጨዋታ ቡድኖቹ እልህ አስጨራሽ የመሸናነፍ ጥረቶችን አስመልክተውን የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ወደ ጎልነት የሚደረጉ ሙከራዎች በእጅጉ የሳሱበት እንደነበር መታዘብ ችለናል።
አሰልጣኝ መሠረት ማኔ ከዕረፍት መልስ ባደረገቻቸው ቅያሪ ወደ ሜዳ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስተው በገቡ ተጫዋቾች ጎሎች ተገኘው ኤሌክትሪክ እንዲያሸንፍ አድርጎታል። በዚህም 73ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የመስመር ተሻጋሪ ኳስ የሽታዬ ሲሳይ ድንቅ ብቃት ታክሎበት ያገኘችውን ኳስ ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተመልሳ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባቸው ትንቢት ሳሙኤል አስቆጥራ ቡድኑ መሪ እንዲሆን አስችላለች። ጎል ለማስተናገድ በመገደዳቸው የተጫዋች ለውጥን አድርገው አቻ ለመሆን ድሬዳዋዎች ጥረት አድርገው ታትተዋል 83ኛው ደቂቃ ላይ ፎዚያ መሐመድ ወደ ሳጥን ስትመታ ኳስ በእጅ ተነክቷል በማለት የድሬዳዋ ተጫዋቾች ቅሬታ ቢያሰሙም የዕለቱ ዳኛ ሳትሰጥ በመቅረቷ ድሬዳዋዎች በዳኛዋ ላይ ክስ አስመዝግበዋል። ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ የድሬዳዋ ተከላካዮች ፍፁም ስህተት የታከለበትን አጋጣሚ ተቀይራ የገባችው አይናለም አሳምነው በአግባቡ ተጠቅማበት ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 የበላይነት በመጨረሻም ተጠናቋል።