የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ የተካሄዱ ሲሆን መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን የረቱበትን ድል አስመዝግበዋል።
የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ ሊጠናቀቅ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል። 11ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የሊጉ ጨዋታዎች ትላንት በሦስት መርሀግብሮች የጀመረ ሲሆን ዛሬም በተመሳሳይ ሦስት ጨዋታን አስተናግዶ ተገባዷል። ትላንት ረፋድ 4 ሰዓት ሲል ይርጋጨፌ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቶ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኤሌክትሪክ 16ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር አጥቂዋ ሰላማዊት ጎሳዬ ከመረብ ባሳረፈችው ብቸኛ ጎል ሦስት ነጥብን በመሸመት በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ መቀመጥ ችለዋል።
ትላንት ከሰዓት የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ያለ ጎል ተጠናቀዋል። አስቀድሞ ከቀትር በኋላ ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክርን ያሳየ ቢሆንም ግብ ሳይቆጠርበት ሲፈፀም ቦሌ ክፍለ ከተማ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታም ኳስ እና መረብ መገናኘት ሳይልችሉ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።
የ11ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ ሶስት ነጥብን ያገኙ ክለቦች ሆነዋል። 4 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተገናኝቶ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ቡድኑን ባለ ድል አድርጎ ተጠናቋል። ንፋስ ስልኮች በመጀመሪያው አጋማሽ 7ኛው ደቂቃ ላይ እየሩሳሌም ታደለ ባስቆጠረችው ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ከዕረፍት መልስ ብልጫን በጨዋታው ላይ ማሳየት የቻሉት እንስት ፈረሰኞቹ በዓይናለም አለማየሁ እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ ላይ በገብርኤላ አበበ ተጨማሪ ጎል 2ለ1 በማሸነፍ ወሳኝ ድል አሳክተዋል።
በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመሩት የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በድሬዳዋ ከተማ ተቸግረውም ቢሆንም በማሸነፍ መሪነታቸውን አስፍተዋል። ገና ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንክ በመዲና ዐወል ጎል ቀዳሚ መሆን ሲችል 27ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ተጨማሪ ጎል አክላ የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች። ድሬዳዋ ከተማዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በስራ ይርዳው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል አግኝተዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ወሳኟ አጥቂ ሎዛ አበራ በጉዳት በመሳይ ተመስገን ተቀይራ ወጥታለች። ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በሎዛ አበራ ተቀይራ የገባችው መሳይ ተመስገን በድሬዳዋ ተጫዋች ላይ በሰራችው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ስትወገድ 74ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ለራሷ ሁለተኛ ለክለቧ ሶስተኛ ግብን ከመረብ አዋህዳ ጨዋታው በንግድ ባንክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በመቻል እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል ተደርጎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደካማ የውጤት ማሽቆልቆል እየገጠመው የሚገኘው መቻል በአዲስ አበባ ከተማ በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ መንገድ 89ኛው ደቂቃ ተቀይራ በገባችው አስራት አለሙ ጎል ተቆጥሮባቸው 1-0 መረታት ችለዋል።