አሸናፊ በቀለ አዲሱ የዐፄዎቹ አሰልጣኝ ሲሆኑ ረዳት አሰልጣኛቸውንም ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብቅ ብለው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ከቻሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የሊግ ውድድር ላይ ቡድኑ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ላይ ካስመዘገበው ደካማ አቋም የተነሳ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽን ከኃላፊነት በማሰናበት በይፋ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን የቡድኑ አሰልጣኝ በማድረግ ሾሟል።
በሊጉ በተደረጉ አስራ ሶስት ጨዋታዎች በ17 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ክለቡ የቀድሞ መከላከያ ፣ ንግድ ባንክ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ የነበሩት አሸናፊ በቀለ ከሰሞኑ ከፋሲል አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት በመጨረሻም በመስማማታቸው አሰልጣኙ ክለቡን በዛሬው ዕለት ልምምድ ማሰራት የጀመሩ ሲሆን በሀድያ ሆሳዕና እና ጅማ አባጅፋር ረዳት አሰልጣኝ ሆነው የሰሩት እያሱ መርሀፅድቅ (ዶ/ር) በረዳት አሰልጣኝነት አብረዋቸው እንደሚሰሩ ተመላክቷል። ለሁለቱም አሰልጣኞች የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር በትላንትናው ዕለት በጎንደር ከተማ አቀባበል አድርጎላቸዋል።