በኢትዮጵያ እና በሞዛምቢክ መካከል የተደረገው የምድብ አንድ ሁለተኛ ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የበላይነቱን ሲወስድ የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራም 14ኛው ደቂቃ ላይ አድርጓል። በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የወሰዱትን ኳስ ግራ መስመር ላይ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳጥን ውስጥ ለነበረው ከነዓን ማርክነህ አመቻችቶ ቢያቀብልም ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ከነዓን ማርክነህ ያደረገውን ሙከራ የአጨራረሱ ድክመት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ቪክቶር አልኪኖ ጓምቤ መልሶበታል።
በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዋልያዎቹ 21ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። አማዱ ሞሜድ ጋቶች ፓኖም ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት መስዑድ መሐመድ ሲያሻማ በሌሎች ተጫዋቾች ተጨርፎ ያገኘው ሚሊዮን ሰለሞን ወደ ግብ ሲሞክር ተከላካዮቹ መልሰውበታል። ያንኑ ኳስ ያገኘው እና ለማስቆጠር አመቺ ቦታ ላይ የነበረው ፉዐድ ፈረጃ ግን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ይህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል ትልቁ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው እና ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ሞዛምቢኮች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በተሳኩ የኳስ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የሚደርሱት ግን አጨራረስ ላይ ድክመት የሚታይባቸው ኢትዮጵያዊያን የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሴኮንዶች ሲቀሩ ትልቅ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ቸርነት ጉግሣ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል በዘገየ ውሳኔ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ቪክቶር ጓምቤ መልሶበታል።
በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ ከኳስ ቁጥጥራቸው ውጪ ተቀዛቅዘው እና እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ሲቸገሩ 50ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሣ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ከማቀበል አማራጭ ጋር ጥሩ ኳስ ቢያገኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ይህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል የተፈጠረ ሌላኛው ትልቅ የግብ ዕድል ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ከተጫወቱበት አጨዋወት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ አቀራረብ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት እና የተሻሉ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ሞዛምቢኮች 67ኛው ደቂቃ ላይ ንፁህ የግብ ዕድል አባክነዋል። ሳጥን ውስጥ የዓየር ላይ ኳስ ያገኘው አይዛክ ካርቫልሆ በግንባሩ ቢገጭም የአጨራረሱ ድክመት ተጨምሮበት ዒላማውን ስቶበታል። እንደፈጠሩት የግብ ዕድል ግብ ማስቆጠር የነበረባቸው ዋልያዎቹ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ በዱሬሳ ሹቢሳ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።