👉 \”በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል ፤ ማሸነፍም ይገባቸዋል\”
👉 \”በመጀመሪያው ጨዋታ እና በሁለተኛው ጨዋታ የሰራናቸው ነገሮች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል\”
👉 \”…ግን እኛ በእጃችን ያለውን ጨዋታ ማሸነፍ ነው ያለብን። ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ስለሆነው ነገር ምንም ማድረግ አንችልም\”
በቻን ውድድር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአዘጋጇ ሀገር አልጄሪያ ጋር ያደረገችውን ፍልሚያ አንድ ለምንም በሆነ የሽንፈት ውጤት ማገባደዷ ይታወቃል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በዋልያው በኩል አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
\”የአልጄሪያ ተጫዋቾች ከእኛ የተሻለ ከመጀመሪያው ጨዋታ የሚያገግሙበት አንድ ቀን ስላገኙ ትኩስ ጉልበት ነበራቸው። እነሱ ሜዳ ላይ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ። ይህንን ተከትሎ ጨዋታው ለእኛ ከባድ ነበር። ጥሩ ተጫውተዋል። በዚህ አጋጣሚ አልጄሪያዎች ወደ ቀጣዩ ዙር ስላለፉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው።
\”በተለይ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ተጭነው ጫና ውስጥ እየከተቱን ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም የግብ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር ፤ ከዚህ በኋላ ግን እኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል። ከእነሱ የመጣው ጫና የሚጠበቅ ነው ፤ ምክንያቱም ባለሜዳ ቡድን ስለሆኑ። የሆነው ሆኖ መጨረሻ ላይ ተሸንፈን ወጥተናል።\”
ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላቸው ዕድል ጠበብ ያለባቸው ዋልያዎች በቀጣይ ከውድድሩ ውጪ መሆኗን ከወዲሁ ካረጋገጠችው ሊቢያ ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ በተመለከተ \”ወረቀት ላይ ሲታይ አልጄሪያ 6 ነጥብ አግኝታ ከወዲሁ አልፋለች። ሞዛምቢክ ደግሞ አራት ነጥብ አላት። ይህንን ስትመለከት ከበድ ይላል። ግን እኛ በእጃችን ያለውን ጨዋታ ማሸነፍ ነው ያለብን። ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ስለሆነው ነገር ምንም ማድረግ አንችልም። ዛሬ ቢያንስ አቻ ብንወጣ ኖሮ ለእኛ ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ በመጀመሪያው ጨዋታ እና በሁለተኛው ጨዋታ የሰራናቸው ነገሮች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል።\”
በማስከተል በስታዲየሙ ስለነበረው የደጋፊ ድባብ የተጠየቁት አሠልጣኝ ውበቱ \”በስታዲየም የነበረው ተመልካሽ ከ39 ሺ ይበልጣል። ስታዲየሙን የሞሉት ደጋፊዎች በሚገርም ሞራል ከተጫዋቾቻቸው ጎን ሆነው ሲደግፉ ነበር። ተጫዋቾቹም በድጋፉ እየተበረታቱ በደንብ ሲሮጡ ነበር። ደጋፊው ለቡድኑ ጥሩ አበርክቶ ነበረው። ለእንደእኛ አይነት ቡድን ትንሽ ጫና ነበረው ፤ አንዳንዶቹ ተጫዋቾቻችን እንደዚህ አይነት ልምድ የላቸውም። በአጠቃላይ ደጋፊዎቹ ጥሩ ድጋፍ አርገዋል ፤ በጨዋታውም እንደተዝናኑ አስባለው። እንኳን ደስ አላችሁም ማለት እፈልጋለው። በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል ፤ ማሸነፍም ይገባቸዋል።\”
በመጨረሻ ጨዋታው ሊገባደድ ሲል ውጤቱን ሊለውጥ የሚችል ዕድል ከነዓን አግኝቶ ያልተጠቀመበት አጋጣሚ እንደተለመደው ቡድኑ ማምከኑ አስቆጪ እንደነበር ገልፀው የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ፈፅመዋል።