ቀጣዮቹ የሊጉ ጨዋታዎች መከወኛ ቀናት ከወትሮ ለምን ለውጥ ተደረገባቸው?

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ-ግብር መከወኛ ቀናት ላይ ስለተደረገው ማስተካከያ የሊጉን የበላይ አካል ጠይቀን ተከታዩን ምላሽ አግኝተናል።

የሀገራችን ብሔራዊ ቡድን በ7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ላይ መሳተፉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ላይ መቋረጡ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድናችን ከውድድሩ ውጪ ከሆነ በኋላ አሁን ትኩረቶች ሁሉ ወደ ሊጉ የዞሩ ሲሆን አክሲዮን ማኅበሩም የተስተካካይ ሳምንት ጨዋታዎችን ጨምሮ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከ14ኛ እስከ 19ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉትን ጨዋታዎች መርሐ-ግብር ይፋ አድርጓል።

\"\"

ይፋ በሆነው መርሐ-ግብር ላይ ደግሞ የአንድ ሳምንት አራት የጨዋታ ቀናት ሀሙስ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ እንደሚደረጉ ታውቋል። ከዚህ በፊት በጨዋታ ሳምንታት መካከል ሁለት የእረፍት ቀናት የነበሩ ሲሆን አሁን ግን የእረፍት ቀናቱ ወደ ሦስት አድጓል። ይህ ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት ለማጣራት ሞክረን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

\"\"

\”መርሐ-ግብሩን ስናወጣ የመጫወቻ ቀኖቹ በዚህ መንገድ የተመረጡት ለተመልካቾች ምቹ እንዲሆኑ ታስቦ ነው። ከዚህ በፊት በአዘቦት ቀናትም በአብዛኛው ጨዋታዎች ይደረጉ ነበር። ይህ ደግሞ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም መጥተው ጨዋታዎችን የሚመለከቱበትን ዕድል ያጠባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት እንደገለፅነው የውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ባለመብት ስታዲየሞች በተመልካቾች እንዲሞሉ የቀደመ ጥያቄም ስለነበረው መርሐ-ግብራችን ላይ የቀናት ለውጦችን ለማድረግ ችለናል። ስለዚህ አሁን በወጣው መርሐ-ግብር ሁሉም የጨዋታ ቀናት ከሀሙስ እስከ እሁድ የሚደረጉ ይሆናል።\” ብለዋል።