የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና ሀዲያ ሆሳዕናን አለመስማማት ተከትሎ የቀረበውን ይግባኝ የተመለከተው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ አስተላልፏል።
ሀዲያ ሆሳዕና በተጠናቀቀው የ2014 የውድድር ዓመት በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እየተመራ እንደነበር አይዘነጋም። የውድድር ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን አሠልጣኙ እና ክለቡ ከውል ስምምነት ማቋረጥ ጋር በተያያዘ አለመስማማት ውስጥ የነበሩ ሲሆን ጉዳያቸውም ወደ ሀገሪቱ የእግርኳስ የበላይ አካል አምርቶ ሲመረመር ቆይቶ ነበር። ጉዳዩን የያዘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም ጥቅምት 23/2015 ሀዲያ ሆሳዕና እግርኳስ ክለብ ለአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ያልከፈለውን የሰኔ እና ሐምሌ 2014 ደሞዝ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲከፍል አለበለዚህ ከተጫዋቾች ምዝገባ እና ዝውውር እንዲታገድ ውሳኔ ማስተላለፉን ዘግበን ነበር። ከውሳኔው በኋላ ሀዲያ ሆሳዕና የተላለፈው ውሳኔ እንዲነሳለት አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ደግሞ የሁለት ወር ብቻ ሳይሆን እስከ ውላቸው ማብቂያ ድረስ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጥያቄያቸውን አቅርበው ተከታዩ ውሳኔ መሰጠቱን የአሠልጣኙን ጉዳይ የያዙት የህግ አማካሪ እና ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ገልፀውልናል።
ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም ጥቅምት 23 የተወሰነውን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ በከፊል ሽሯል። በዚህም ለአሠልጣኙ የሁለት ወር ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው እና ስንብቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ተብሎ የተወሰነው የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ የውል ድንጋጌውን የሚጥስ ስለሆነ በከፊል እንዲሻር ተደርጎ ይህ ውሳኔ እስከተሰጠበት ቀን (ጥር 15/2015) ድረስ ክለቡ ለአሠልጣኙ ደሞዝ እንዲከፍል ታዟል። ከዚህ በተጨማሪም በቀጣዮቹ አምስት የስራ ቀናት በአሠልጣኙ እና ክለቡ እንዲሁም አንድ የጋራ ገለልተኛ ተወካይ ተሰብስበው ጉዳዩን በስምምነት እንዲጨርሱ ተወስኗል። ክለቡ ግን ጉዳዩን በስምምነት ለመጨረስ ፍቃደኛ ካልሆነ እስከ ውሉ ፍፃሜ ድረስ አሠልጣኙን እንዲያሰራ ተገልጿል።
ክለቡ ይህ ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀናት ውስጥ ውሳኔዎቹን ተፈፃሚ የማያደርግ ከሆነ ከውድድር እንዲታገድ እና ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት ግልጋሎይ እንዳያገኝ ተወስኗል።