ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በዝውውር ተሳትፎው ቅድሚያውን የሚወስደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን በማስፈረም ዝውውሩን አገባዷል።

በሁለተኛው ዙር ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የነቃ ተሳትፎን ለማድረግ ከሀገር ውስጥ አብዱራህማን ሙባረክ ፣ አማረ በቀለ እና ነፃነት ገብረመድህንን ከሀገር ውጪ ከኤርትራ የመስመር አጥቂው ዮናስ ሰለሞንን በይፋ የስብስቡ አካል ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻው የዝውውር መዝጊያን በሁለት የውጪ ዜጋ ተጫዋች ቋጭቷል።

\"\"

አንድ ሜትር ከሰማንያ አምስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው የቤኒን ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂው ሸሪፍ ዳይን አካካፖ ሁለተኛው የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሆኖ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሏል። ለሀገሩ ቡፍልስ ቦርጉ እና በቡሩኪናፋሶው ሳሊታስ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ ነው መዳረሻው ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሆን የቻለው።

ቡድኑን የተቀላቀለው ሌላኛው ተጫዋች የ28 ዓመቱ ናይጄሪያዊ አጥቂ ቺሶም ቺካትራ ነው። የክለብ ህይወቱን በሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ ፣ በግብፆቹ ኤልጉና ፣ ጋይሽ ኤፍ ሲ ፣ ናፍት ሚሳን እና ዱሁክ ኤ ኤስ ሲ ፣ በህንድ ለጎኩላም ፣ በኦማን ጆርዳን ለአልፋይሳሊ እና ለሀገሩ ክለቦች አኩዋ ዩናይትድ እና ያለፉትን ዓመታት ደግሞ በአቢያ ዋሪየርስ ሲጫወት ቆይታን አድርጎ የሀገራችንን ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሏል።

\"\"