የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በ11 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲካሄድ ከሦስቱ መሪዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ድል ቀንቶታል።
በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙ ዓለም
የጠዋት ጨዋታዎች
ባህርዳር ላይ የምድብ \’ሀ\’ የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡናን ከአዲስ ከተማ ሲያገናኝ በኳስ ቁጥጥሩና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል አዲስ ከተማዎች ብልጫውን ሲወስዱ የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን አቦሎቹ የተሻሉ ነበሩ። 34ኛው ደቂቃ ላይ የቤንች ማጂው ኤፍሬም ታምሩ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዘላለም በየነ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የላዩ አግዳሚ ሲመልስበት በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ኤፍሬም ታምሩ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዲስ ከተማዎች የተሻለውን ሙከራ ወደ የአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በዚህም ጳውሎስ ከንቲባ በግሩም ዕይታ ከግራ መስመር አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አህመድ አብዱ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው መስፍን ሙዜ ሲመልስበት ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ኳሱን ያገኘው ያሬድ ዓለማየሁ ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስም እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት አዲስ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር ብልጫቸው ላይ የተሻሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲጨምሩ 69ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታዋን መምራት ጀምረዋል። በጥሩ የኳስ ቅብብል የወሰዱትን እና ያሬድ ዓለማየሁ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አሸናፊ በቀለ በጥሩ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተጭነው መጫወት የጀመሩት ቤንች ማጂዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በሀሰን ሁሴን አማካኝነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።
በምድብ \”ለ\” ጅማ ላይ በደብረብርሃን እና በጉለሌ መካከል በተደረገው የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የዳኛ ታደሰ ምንያህልን ድንገተኛ ሕልፈት አስመልክቶ የሕሊና ጸሎት በማድረግ ሲጀመር የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ እና ለተመልካች ሳቢ ያልሆነ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በግራው የማጥቃት ክፍላቸው የተሻለ የተንቀሳቀሱት ደብረብርሃኖች 12ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሌ እሸቱ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ጉለሌዎች በሄኖክ ፍስሃ ፣ ጁንዴክስ አወቀ እና ዳንኤል አፈራው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ቢያደርጉም በደብረ ብርሃኑ ግብ ጠባቂ ደረጄ አለሙ መክኖባቸዋል።
ሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ጉለሌዎች በሄኖክ ፍስሃ ፣ ጁንዴክስ አወቀ ፣ አትርሳው ተዘራ እና ፉዐድ ሱልጣን የጎል ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በተለይ ፉዐድ ሱልጣን የሞከረው እና ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ቢደርሱም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የተቸገሩት ደብረ ብርሃኖች 88ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሌ እሸቱ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።
ከሁለቱ ምድቦች አንፃር በአንድ ሰዓት ዘግየት ብሎ በጀመረው የምድብ \’ሐ\’ የሀምበሪቾ ዱራሜ እና ስልጤ ወራቤ ጨዋታ ልክ እንደተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ጥዑመልሳን ሀ/ሚካኤል ግብ አስቆጥሮ በጊዜ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀምበሪቾ ዱራሜ የተቆጠረባቸውን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር ቀላል አልሆነላቸውም። የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ግን እንዳሻው ጫሚሶ ግብ አስቆጥሮ ሀምበሪቾ ዱራሜን አቻ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለበት እና በሁለቱም በኩል የመፈራራት ስሜት የተመለከትንበት ሲሆን በአጋማሹም በሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግብ ለመድረስ አማራጭ አርገው ተጠቅመዋል። ይህም ፍሬያማ ሳይሆን ምንም ግብ ሳይቆጠር ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩት ግቦች ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።
የ05፡00 ጨዋታዎች
በምድብ \’ሀ\’ ባህርዳር ላይ ሰንዳፋ በኬን ከሀላባ ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቃዛ እና የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል የተሻሉ የነበሩት ሰንዳፋዎች እንዳለ ፀጋዬ እና የአብሥራ በለጠ ከሳጥን ውጪ ባደረጓቸው ሙከራዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ሲጀምሩ 20ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። መሳይ ሰለሞን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ጥሩ ቅብብል ቢያደርጉም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ እጅግ የተቸገሩት ሀላባዎች የተሻለውን ሙከራ 43ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት በሰዒድ ግርማ አማካኝነት አድርገዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 65ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ሰለሞን ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መልሶበታል። ካለፉት ጨዋታዎች ተቀዛቅዘው የቀረቡት በርበሬዎቹ 79ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ሙሉቀን ተሾመ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ምስጋና ግርማ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላም የሚጠቀስ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።
ጅማ ላይ ሻሸመኔን ከከፋ ቡና ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሻሸመኔ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የበለጡ ሲሆኑ በተቃራኒ ሜዳ ላይ ግን እምብዛም ስል ሳይሆኑ ለከፋ ቡና ጠንከር ያለ የመከላከል አጨዋወት እጅ ሰጥተው የጠራ የግብ ማግባት ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ከፋ ቡናዎች በበኩላቸው በጨዋታው በተለየ መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበትን አጨዋወት ሲከተሉ የነበረ ሲሆን በመከላከሉ እና በማጥቃቱ እንደቡድን በመንቀሳቀስ በተለይ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ይህ ውጥናቸው ሰምሮም በ38ኛው ደቂቃ አለምገና አሰፋ ጎል አስቆጥሮ አጋማሹን እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ሻሸመኔ በብዙ መስፈርቶች የተሻሉ ቢሆኑም በማጥቃቱ በኩል የጎል እድል መፈጠር ላይ እጅግ ደካማ ሆነው ታይተዋል። በጌትነት ተስፋዬ እና በዮናስ ባቤና የጎል ሙከራ ቢያደርጉም በከፋ ቡናው የግብ ጠባቂ ሙከራቸው ጎል ሳይሆን ቀርቷል። ከፋ ቡና በሁለተኛ አጋማሽ በመከላከሉ አተኩረው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በመልሶ ማጥቃቱ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በመጠኑ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት የመከላከል አጨዋወት ተሳክቶላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠሩትን ጎል አስጠብቀው ወጥተዋል።
የ08፡00 ጨዋታዎች
ባህርዳር ላይ ጋሞ ጨንቻን ከምድቡ መሪ ንግድ ባንክ ጋር አገናኝቷል። በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ባንኮቹ 11ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አብዱለጢፍ ሙራድ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ብፁዕአምላክ ማስቆጠር ችሏል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በሚያገኙት ኳስ ወደፊት ለመሄድ የሚጥሩት ባንኮች 27ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊ ዓባይ ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ባደረገው እና ግብጠባቂው ባስወጣው ኳስም ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ከዚህች ቅፅበት በኋላ ግን ጋሞዎቹ በእንቅስቃሴ ደረጃ በደንብ ሲሻሻሉ 28ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አማኑኤል ተፈራ ወደ ሳጥኑ የቀኝ ክፍል በግሩም ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ለለገሠ ዳዊት ሲያቀብል ለገሠ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው አላዛር ማረኔ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ያገኙት ጨንቻዎች ግን ሳይጠቀሙበት ቀርተው ትልቅ የግብ ዕድል አባክነዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያ 25 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፍጹም የበላይነቱን ሲወስዱ 54ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከሳጥን ውጪ ባስቆጠራት ድንቅ ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም አብዱለጢፍ ሙራድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን እና ግብጠባቂው ሳይቆጣጠረው የቀረውን ኳስ ያገኘው በረከት ግዛቸው በደረሠበት አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ባንኮቹ ያለማቋረጥ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 69ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠረው እና የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ አብዱለጢፍ ሙራድ ከሳጥን አጠገብ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ንጉሤ ሙሉጌታ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ግን የሚታወቁበትን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ እጅግ የተቸገሩት ጋሞዎች በተሻለ ሁኔታ ተጭነው ሲጫወቱ 73ኛው ደቂቃ ላይ ለባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ አስቆጥረዋል። በፍቃዱ ሕዝቅኤል ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አምበሉ በለጠ በቀለ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮታል። የጨዋታው መጠናቀቂያ 95ኛው ደቂቃ ላይም የጋሞው ቃለአብ በቀለ ግሩም ሙከራ አድርጎ የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 27 በማድረስ የምድብ መሪነቱን አጠናክሯል።
በምድብ ለ የቂርቆስ ክ/ከተማ እናጅንካ ጨዋታ በተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ ፈጣን ጎል በአብዱ መጂድ ሁሴን አማካኝነት ተቆጥሮ ቂርቆሶች መምራት ጀምረዋል። ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም በተቀሩት ደቂቃዎች ጅንካዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን ሲያደርጉ ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉት መሪዎቹ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብዙም ማድረግ ባይችሉም በ33ኛው ደቂቃ ላይ በክብሮም ፅዱቅ ሙከራ ሲያደርጉ በተቀረው ደቂቃዎች ሙከራ ማድረግ ተስኖቸዋል። ጅንካ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢሞክሩም በቂርቆሶች ጠንካራ እንቅስቃሴቸው ሲገታ ነበር። በመልሶ ማጥቃቱ በተደጋጋሚ ቂርቆስ የግብ ክልል ቢደርሱም አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸዋል። በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ግን በኢትዮ ሎሳንጉሌ አማካኝነት የአቻነቷን ጎል ማስቆጠር ችለዋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ቂርቆስ ከተማ ከመጀመሪያ አጋማሽ ተሻሽሎ በመቅረብ ኳስ በመቆጣጠር የበላይ ሲሆኑ ብልጫ እንደመውሰዳቸው አንፃር የጎል እድል መፍጠርም ሆነ የጎል ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። በመጀመሪያ አጋማሽ ያገኟትን የጎል አጋጣሚዎች ባለመጠቀማቸውም በሁለተኛ አጋማሽ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ጅንካዎች ቂርቆሶች ኳስ ይዘው እንደሚጫወቱ በመረዳት በመከላከል እና እንቅስቃሴዎቻቸውን በማበላሸት መጫወትን የመረጡ ሲሆ በመልሶ ማጥቃት እና ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ነበሩ። በተደጋጋሚ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ በቂርቆስ ግብ ጠባቂ ምክንያት ወደ ጎል መቀየር ባይችልም በ90ኛው ደቂቃ ላይ በኑር ሀሰን አማካኝነት የማሸነፊታውን ጎል አስቆጥረው ሦስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።
ዳሞት ከተማ እና ነጌሌ አርሲ ሆሳዕና ላይ በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ጥሩ እንቅስቀሴ ሲያደርጉ ነበር። በከፍተኛ አልሸነፍ ባይነት እና ትንቅንቅ የተሞላበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ላይ ግብ ሳይቆጠርባቸው ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲታይ የግብ ሙከራዎችም ተበራክተዋል። በ65ኛ ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን የግብ ዕድል ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ሳምሶን ቁል በግንባር በማስቆጠር ዳሞት ከተማን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ነጌሌ አርሲዎች ግብ ለማስቆጠር የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የዳሞት የኋላ መስመር በጠንካራ መከላከል ያገኙትን የግብ ብልጫ አስጠብቆ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።
የ10፡00 ጨዋታዎች
ባህር ዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ በአቃቂ ቃሊቲ እና ወሎ ኮምቦልቻ መካከል በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር ሲያስተናግድ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራም 31ኛው ደቂቃ ላይ በአቃቂ ቃሊቲዎች ተደርጓል። ኪሩቤል ይጥና በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻማ ያገኘው ቢኒያም ሲራጅ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። ይሁን እና በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መድረስ የቻሉት ኮምቦልቻዎች በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ሳጥን ያስገቡትን ኳስ በሌሎች ተጫዋቾች ተጨርፎ ያገኘው ሰለሞን ጌዲዮን ማስቆጠር ችሏል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ ወሎ ኮምቦልቻዎች አስደናቂ የሆነ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ኳሱን በግሩም ሁኔታ ገፍቶ መውሰድ የቻለው ዮናታን ኃይሉ በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮት የክለቡን መሪነት አጠናክሯል። ከሚታወቁበት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተለየ ተዳክመው የቀረቡት አቃቂዎች የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ሲቀሩ ካለፉት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ወሎዎች ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። ጨዋታውም በወሎ ኮምቦልቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጅማ ላይ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በእንጅባራ ከተማ እና በንብ መካከል ተደርጓል። እንጅባራዎች መሀል ሜዳ ላይ ተጫዋች በማብዛት ኳሱን መቆጣጠር እና መጫወት ሲችሉ ከቀኝ መስመር በረጅም ኳስ በመጣል ለመጠቀም ቢሞክሩም አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ንቦች ከዚህ ቀደም በነበሩት ጨዋታዎች የነበራቸው እንቅስቃሴ ዛሬ ቀንሶ ሲታይ በመልሶ ማጥቃት በጥቂቱ ወደ ፊት ሲሄዱ ቢታየም በእንጅባራ ተከላካዮች በቀላሉ ኳስ ሲነጠቁ ይስተዋል ነበር።
በሁለተኛው እንደተጀመረ በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ታይቷል። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ እንጅባራዎች በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸውን የኳስ ብልጫ መውሰድ ሲያቅታቸው ተስተዋውለዋል። ኳስ ሚይዙበት ጊዜ በረጅም የመልሶ ማጥቃት ሲያጠቁ በሁለተኛ አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባያደርጉም በ80ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ትኩሱ ጌታቸው በግሩም አጨራረስ በግንባር በመግጨት ጎል ማስቆጠር ችሏል። ንቦች በሁለተኛ አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡ ሲሆን ለደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢኖራቸውም በተቀሩት ብልጫ ሲወስዱ አብዛኛውን ኳስ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ይዘው ቢጫወቱም ለጎል የሚሆን ዕድል መፍጠር እና የእንጅባራ ተከላካዮች ነፃነት ባለመስጠታቸው ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በጭማሪ ደቂቃዎች በእንጅባራ ተከላካይ ተስፋፂሆን ፋንቱ እና የንቡ ኪም ላም የዓየር ኳስ ለመሻማት ሲሞክሩ በተፈጠረ ግጭት በስታዲየም ውስጥ ያለ ተመልካች እና በሁለቱም ቡድኖች እጅግ ያስደነገጠ ጉዳት ተፈጥሯል። በሁለቱም ቡድኖች ከተመልካች በቀይ መስቀል በመላው እስፖርት ወዳዱ ህዝብ ጋር በመተጋገዝ የንብ ተከላካይ ኪም ላም ህክምና ተደርጎለት ወደ ጨዋታው ሲመለስ የእንጅባራው ተስፋፂሆን ፋንቱ በመጀመሪያ ህክምና ተደርጎለት ከጉዳቱ ቢመለስም ተጨማሪ ህክምና ስለሚስፈልገው ወዲያውኑ ወደ ህክምና ጣቢያ አመርቷል። ጨዋታውም በቀዘቀዘ ስሜት ሲቀጥል እንጅባራዎች በከላከል ውጤታቸውን በማስጠበቅ ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቋሉ።
ይየምድብ \’ሐ\’ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በየካ ክ/ከተማ እና ገላን ከተማ መሀል ተካሂዷል። የመጀመሪያ አጋማሽ ለዐይን ሳቢ እና ለተመልካች አዝናኝ የሆነ በኳስ ቁጥጥር እና በዛ ባለ የግብ ሙከራ የታጀበ አጋማሽ ነበር። በአጋማሹ የተወሰነ ደቂቃ የካ ክ/ከተማ የበላይነቱን የሚወስድ ሲሆን በተራ ደግሞ ገላን ከተማ የበላይነቱን ተረክቦ ጫና ሲፈጥር ተመልክተናል። ሆኖም በአጋማሹ ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑ ረጃጅም ኳሶች የተመለከትን ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ የበለጠ ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ የነበረው አጋማሽ ነበር። ጨዋታውም በዚህ አጨዋወት እየሄደ በ76ኛው ደቂቃ የገላን ከተማ ድንቅ ተጫዋች ጥሩ ግብ በማስቆጠር ገላን ከተማዎችን መሪ ማድረግ አስችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በቀራቸው 15 ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት የካዎች በገላን ከተማዎች የኋላ ክፍል ተበልጠው ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ሽንፈት ማስተናገድ የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ገላን ከተማዎች ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።