ሪፖርት | የየኋላሸት ሰለሞን ብቸኛ ጎል ሠራተኞቹን ባለ ድል አድርጋለች

ከተያዘለት ደቂቃ ዘግይቶ የጀመረው የወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የምሽቱ ጨዋታ በሠራተኞቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

01፡00 ሲል ጨዋታው ይጀመራል ተብሎ ቢጠበቅም አስራ አምስት ደቂቃዎችን ዘይግቶ ነበር ጅምሩን ያደረገው። ምክንያቱ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ቀደም ብሎ ካስመዘገበው ትጥቅ ውጪ ተቃራኒውን ለመጠቀም ሜዳ ላይ ይዞ መገኘቱ የመዘግየቱ መነሻ ሆኗል። የሆነው ሆኖ ወልቂጤዎች ከሆቴላቸው አስመዝግበውት የነበረውን ትጥቅ ካስመጡ በኋላ በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን በህሊና ፀሎት በማሰብ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት በመራው ሔኖክ አበበ ማሪነት ተጀምሯል።

\"\"

ወላይታ ድቻዎች ከቀናት በፊት ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት የተስተካካይ ጨዋታ ላይ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ወደ ሜዳ ገብተዋል። የምሽቱ መርሀግብር የመጀመሪዎቹ አስር ደቂቃዎች ምንም እንኳን ግልፅ የሆኑ የጎል ሙከራዎች ተፈጥረው መመልከት ባንችልም ፈጣን የሆኑ እና ፋታ የለሽ እንቅስቃሴን በሁለቱም በኩል ተመልክተናል።


ጨዋታው ቀጥሎ ብዙም ሳይጓዝ 12ኛው ደቂቃ ላይ እንደ ደረሰ በጥሩ የጨዋታ መንገድ ከመስመር የተሻገረን ኳስ ተጠቅሞ አጥቂው የኋላሸት ሰለሞን ወልቂጤ ከተማን መሪ አድርጓል። ወልቂጤ ከተማዎች ገና በጊዜ ወደ ቋታቸው ጎልን ካስገቡ በኋላ በጥልቀት አፈግፍገው ሲጫወቱ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ከተለያየ የሜዳው ክፍል ርብርብ በማድረግ ጎል ለማስቆጠር ብርቱ ጥረትን ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ጨዋታው ቀጥሎ ወልቂጤ ከተማዎች የኋላ የሜዳቸው ክፍል እንዳይጋለጥ ሽፋን በመስጠት የድቻን የማጥቃት ጉልበት ለመግታት ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን ኳስን በእግራቸው ስር ሲያገኙ ግን በፈጣን መልሶ ማጥቃት በቀኝ በኩል ወደ ተሰለፈው አቡበከር ሳኒ አመዝነው ለመጫወት ጥቂት ጥረት አድርገዋል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫን በተጋጣሚያቸው ላይ ያሳዩ ይምሰል እንጂ የተሳኩ ዕድሎች በማግኘቱ ረገድ ግን ሳይሳካላቸው አጋማሹ ተገባዷል።


ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ወልቂጤ ከተማዎች በወላይታ ድቻ የመከላከል ድክመት አከታትለው ሁለት ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ከተሻጋሪ ኳስ አምበሉ ጌታነህ ከበደ ሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሲመታ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነበት እና ከሁለት ደቂቃዎች መልስ የወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች የሰሩት ግልፅ ስህተት ተጠቅሞ የኋላሸት ሰለሞን ከግቡ ትይዩ የደረሰውን ኳስ ሁለተኛ ጎል አደረገው ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን ወደ ላይ ሰዷታል። ይህቺም አጋጣሚ ወልቂጤዎችን የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቀደም ብለው በዚህኛውም አጋማሽ ጥቃቶች የተሰነዘረባቸው ወላይታ ድቻዎች የጨዋታው ስዓታት በገፉ ቁጥር ግን ቅኝት ውስጥ ለመግባት ጥረት ወደ ማድረጉ ፊታቸውን አዙረዋል ፣ በተለይ አበባየው ሀጂሶ እና ዮናታን ኤልያስን ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ በይበልጥ የወልቂጤን የግብ ክልል መፈተሽ ጀምረዋል። 58ኛ ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳው በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ወጣቱ አጥቂ ቢኒያም ፍቅሬ በነፃነት ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ በግቡ የላይኛው አግዳሚ በወጣበት ቅፅበታዊ ሙከራ ወደ መሰንዘሩ ገብተዋል።


በሌላ ሙከራ ስንታየሁ መንግሥቱ ተቀይሮ ወደ ሜዳ እንደገባ ከማዕዘን የተሻማለትን ኳስ በወልቂጤ ተከላካዮች ተጨራርፋ ከጀርባቸው ሆኖ ያገኛትን ኳስ በመጀመሪያ ንክኪው ወደ ጎልነት ለወጣት ሲባል ጀማል ጣሰው በፍጥነት የያዘበት ሌላኛዋ ሙከራ ነበረች። በወላይታ ድቻ የኳስ ቁጥጥር ድርሻው ቢወሰድባቸውም የሚያገኙትን አጋጣሚዎች ከመጠቀም ወደ ኋላ የማይሉት ወልቂጤ ከተማዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ እና ተከላካዮቹ በሰሩት የቅብብል ስህተት ፈጣኑ አጥቂ የኋላሸት ነጥቋቸው ወደ ጎልነት ለወጠው ሲባል ካስቆጠረው ግብ ውጪ ያገኛትን ሦስተኛ ዕድል መጠቀም ሳይችል አሁንም ቀርቷል።

\"\"

የጨዋታውን የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በይበልጥ በስንታየሁ መንግሥቱ እየታገዙ አቻ ሆኖ ለማጠናቀቅ በብርቱ ቢታገሉም ጥቅጥቅ ባለ አስገራሚ የመከላከል አደረጃጀት አላፈናፉን ያሉትን የወልቂጤ ተከላካዮችን አልፎ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረችው ብቸኛ ግብ በሰራተኞቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።