የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በ14ኛ ሳምንት በተከሰቱ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት ባደረገው ስብሰባ በ14ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በክለቦች አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው ጨዋታ አምስት ተጫዋች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ የ5000 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ስለቀረበ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 50000 ሺ ብር በአጠቃላይ 55 ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።
ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች 15 ደቂቃ ወደሜዳ ዘግይተው ስለመግባታቸው ሪፖርት የቀረበበት በመሆኑ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 25000 ሺ እንዲከፍል እንዲሁም የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት መብት ያለው ድርጅት የካሳ ክፍያ አክስዮን ማህበሩን ከጠየቀ ክፍያውን ሙሉ በሙሉ ክለቡ እንዲሸፍን ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ኮሚቴው የለገጣፎ ለገዳዲ ዋና አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እና የቡድን መሪውን አቶ ኩባ ለማነጋገር ሐሙስ ረፋድ 4:30 በድሬዳዋ ስታዲየም እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉም ታውቋል።