ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ15ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት ላይ ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን የመረጥንበት የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ይህንን ይመስላል።

አሰላለፍ 4-1-3-2

ግብ ጠባቂ


ቢንያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ

በአንደኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለግብ የተለያዩት ወላይታ ድቻዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ላሳኩት አንድ ነጥብ ግብ ጠባቂያቸው ቢንያም ገነቱ ብቃት አስፈላጊ ነበር። በርካታ ሙከራዎች በድንቅ ብቃት በማገድ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው ቢኒያም በተለይም በሦስት አጋጣሚዎች አደገኛ የሚባሉ ሙከራዎችን አምክኗል።

ተከላካዮች


መሳይ አገኘሁ – ባህር ዳር ከተማ

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ምርጫ እየሆነ የሚገኘው መሳይ ቦታውን ለማስከባር እየታተረ ይገኛል። በቀኝ ተከላካይነት ብዙ አማራጭ ባልነበረበት 15ኛ ሳምንትም ቡድኑ ከወላይታ ዲቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ በማጥቃቱም በመከላከሉም ረገድ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ አድርጓል።

\"\"

አሳንቴ ጎድፍሬድ – ድሬዳዋ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ይግጠባቸው እንጂ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ በግሉ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ግብ ጠባቂን ያለፈ ኳስ ከመስመር ላይ ከማውጣት ጀምሮ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ ሳጥን ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አቋርጧል። እንደተጫዋቹ የዕለቱ ብቃት ባይሆን የጨዋታው የ2-1 ውጤት ሊሰፋ ይችል እንደነበር መናገርም ይቻላል።

ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ድሬዳዋ ላይ የ 2-1 ድል ሲቀዳጁ በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው ባይፈተኑም ፍሪምፖንግ ሜንሱ ግን በፈጣን ውሳኔ ቀጠናውን ከአደጋ ነፃ ሲያደርግ የታየበት መንገድ እና ተጋጣሚው ከሦስት የበለጡ ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን እንዳያደርግ ፈተና በመሆን የተሳካ ቀን አሳልፏል። በተጨማሪ አጎሮ ላስቆጠረው የማሸነፊያ ግብም ኳሱን በግንባሩ ገጭቶ አቅጣጫ በማስቀየር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ ወልቂጤን በረታበት ጨዋታ የግራው የቡድኑ ክፍል የአደገኛ ጥቃቶች መነሻ ሆኗል። በጨዋታው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ያስቆጠረው ደስታ የሚያደርጋቸው ቀጥተኛ ሩጫዎች እና ወደ ሳጥን የሚያደርሳቸው ኳሶች ደግሞ ለቡድኑ የግራ መስመር የበላይነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ።

አማካዮች


መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ

ባለብዙ ልምዱ አማካይ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ያሳየበትን ዘጠና ደቂቃ አሳልፏል። ቡድኑ ወልቂጤን ሲረታ አማካይ ክፍል ላይ ቅብብሎችን በማሳለጥም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እና ሙከራዎችን በማድረግ ጎልቶ ወጥቷል። ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሦስት ግቦችም ሁለቱን አመቻችቶ አቀብሏል።

\"\"

ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን

የተረጋጋው አማካይ በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ እንደአብዛኛው ጊዜ ኳስን ቀላል አድርጎ በመጫወት የቡድኑን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ሲመራ ታይቷል። ሁለት ለግብ የሚሆኑ ዕድሎችን ፈጥሮ የነበረው ባሲሩ ዑመር በመጨረሻ ደቂቃ ቡድኑን ለድል ያበቃችውን የያሬድ ዳርዛ ብቸኛ ግብ በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ አቀብሏል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ሱራፌል ባለፈው ሳምንትም ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋራ የጨዋታ ፍሰቱ ማዕከል ሆኖ ሲታይ አንድ ለግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል። አማካዩ በጨዋታው ለግብ ባመቻቸው ኳስ ሌላም የመጨረሻ የግብ ዕድል መፍጠር ችሎ ነበር።

ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ

ወጣቱ የመስመር አጥቂ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀዳሚ ተሰላፊነት ዕድል ባገኘበት የወልቂጤው ጨዋታ ተስፋ እንዲጣልበት የሚያስገድድ ብቃት አሳይቷል። ቡድኑ እሱ በተሰለፈበት መስመር የማጥቃት ሚዛኑ እንዲያጋድል ያደረገ በትጋት የተሞላ የጨዋታ ተሳትፎ ሲያደርግ አዳማን መሪ ያደረገችዋን ጎልም ማስቆጠር ችሏል።

አጥቂዎች


ሳላዲን ሰዒድ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል ባስመዘገበበት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ አንጋፋው አጥቂ በርካታ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የማሸነፊያ ግቧንም በስሙ አስመዝግቧል። በተጨማሪም ቡድኑ ግብ ለማስተናገድ በተቃረበበት ሰዓት ወደራሱ የግብ ሳጥን በመመለስ ግብ ከመሆን ያገደው የኢብራሂም ከድር በግንባር የተገጨ ኳስም በዕለቱ እጅግ የተሳካ ጊዜ ለማሳለፉ ምስክር ነው።

እስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

እንደ ሳላዲን ሁሉ እጅግ የተሳካ ጊዜን ያሳለፈው የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ፈረሰኞቹ ከድሬዳዋ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ላይ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች እና ለቡድን አጋሮቹ የፈጠረው የጨዋታ ነፃነት የሚደነቅ ነበር። የጊዮርጊስን የማሸነፊያ ግብም በጥሩ ቦታ አያያዝ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር የቻለው አጎሮ በተደጋጋሚ ያደረገው የማጥቃት እንቅስቃሴ በቦታው ያለተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

ከደካማ የውድድር ዘመን ጅማሮው ለማገገም እየጣረ የሚገኘው አዳማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3-1 የረታበት አኳኋን አሰልጣኝ ይታገሱን የሳምንቱ ምርጥ ብለን እንድንመርጥ አድርጎናል። ቡድኑ በዲስፕሊን ግድፈት ያጣቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም ወጣቶችን የቀላቀለው የአሰልጣኙ ምርጫ ጨዋታውን በጥሩ ብቃት እንዲጨርሱ ማድረጉ የምርጫችን ምክንያት ሆኗል።

\"\"

ተጠባባቂዎች

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
ተስፋዬ ታምራት – ባህር ዳር ከተማ
ረመዳን የሱፍ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አድናን ረሻድ – አዳማ ከተማ
አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና
ያሬድ ዳርዛ – ኢትዮጵያ መድን
አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ