ድሬዳዋ ከተማ በያሬድ ታደሠ እና አቤል አሰበ ግቦች ሲዳማ ቡና ላይ የ 2-0 ድል ተቀዳጅቷል።
10፡00 ላይ የሲዳማ ቡና እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ሲዳማዎች በ15ኛው ሣምንት ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክን 1ለ0 ከረቱበት አሰላለፍ ቴዎድሮስ ታፈሰን በአቤል እንዳለ ቡልቻ ሹራን በይስሃቅ ካኖ ተክተው ሲገቡ ብርቱካናማዎቹ በተመሳሳይ በ15ኛው ሣምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ብሩክ ቃልቦሬ እና ያሬድ ታደሰ በ አቤል አሰበ እና በሙኸዲን ሙሳ ተተክተው ጀምረዋል።
ጨዋታው ገና በ 2ተኛው ደቂቃ በሊጉ ከታዩ ድንቅ ግቦች መካከል የሚጠቀስ ግብ አስመልክቶናል። ያሬድ ታደሰ ከአሰጋኸኝ ጴጥሮስ የተቀበለውን ኳስ በመግፋት በግምት ከ 25 ሜትር ርቀት ላይ በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ በመምታት እና መረቡ ላይ በማሳረፍ ድሬዳዋ ከተማን መሪ አድርጓል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ተጭነው የተጫወቱት ሲዳማዎች የድሬዳዋ ተከላካዮችን አልፈው ንፁህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ በሩብ ክፍለጊዜውም 6ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ሐብቴ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት 20ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ይገዙ ቦጋለ ካደረጓቸው ደካማ ሙከራዎች ውጪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
የመስመር ተከላካዮቻቸውን እንቅስቃሴ በመገደብ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት መጫወትን የመረጡት ድሬዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ አህመድ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ 28ኛው ደቂቃ ላይም በግብ ጠባቂያቸው ብቃት ባይታገዙ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ይስሃቅ ካኖ ከቀኝ መስመር ለሳላዲን ሰዒድ ያሻገረውን ኳስ ማቋረጥ የቻለው ተከላካዩ ኢያሱ ለገሠ ራሱ ላይ ሊያስቆጥረው ሲል ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በግሩም ቅልጥፍና መልሶታል።
መጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጂ ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት ቡናዎች ወደ ዕረፍት ሊያመሩ ደቂቃዎች ሲቀሩ ሁለት ትልቅ የግብ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። በቅድሚያም 41ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሳላዲን ሰዒድ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲወጣበት ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሰለሞን ሐብቴ ከራሱ የግብ ክልል ከረጅም ርቀት ባሻማው እና የመስመር ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በትክክል ገጭቶ ባላራቀው ኳስ ሳይረጋጋ ከግብጠባቂ ጋር የተገናኘው ይገዙ ቦጋለ በኃይል ወደ ላይ በመላክ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ 66ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር ተከላካዩ መሐመድ አብዱለጢፍ ለግብጠባቂው ለመተው እና ራሱ ለማራቅ በሁለት ሀሳብ ሆኖ በመጨረሻም በዘገየ ውሳኔ ለማራቅ ሲሞክር የሳተውን ኳስ ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ሲመልሰው ያገኘው ይገዙ ቦጋለ ያደረገውን ሙከራም የተሳካ ቀን ያሳለፈው ፍሬው በድጋሚ መልሶበታል።
ጨዋታው በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ 84ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል እንዳለ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ በግንባሩ ሲገጨው ዝግጁ ያልነበረው ተከላካዩ ኢያሱ ለገሠ በተመሳሳይ ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ባይመልሰው ኖሮ ራሱ ላይ ሊያሳርፈው ነበር። ሆኖም ብርቱካናማዎቹ ጨዋታውን የገደሉበትን ግብ 86ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። አብዱለጢፍ መሐመድ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አቤል አሰበ በሚያስደንቅ የመጀመሪያ ንክኪ በማብረድ አስቆጥሮታል።
በመጨረሻ ደቂቃዎችም በተሻለ መነቃቃት ብርቱካናማዎቹ አቤል አሰበ ከሳጥን ውስጥ ባደረገው እና ግብጠባቂው መክብብ ደገፉ በመለሰው ኳስም ተጨማሪ ፈታኝ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ጨዋታውም በድሬዳዋ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ድሬዳዋ ከተማ ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጨዋታውን በጠበቁት መንገድ እንዳላገኙት እና ቀድመው ግብ ማስተናገዳቸው እንዳስቸገራቸው ሲናገሩ ወደግብ ቢቀርቡም መረጋጋት አለመቻላቸውን ውጤት ለማጣታቸው እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ አክለውም ከዕረፍት መልስ ያደረጓቸው ቅያሪዎች ልክ መሆናቸውን ግን ውጤታማ እንዳልነበሩ እና ውድ ሦስት ነጥብ አጥተናል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል። ድል የቀናቸው የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ በበኩላቸው ጨዋታው ካሉበት ደረጃ ከፍ ለማለት ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው እና ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወደራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት እንዳስገደዳቸው በመጨረሻም ግን ለማስተካከል እንሞከሩ እና በቀጣይም በስነልቦና ረገድ ተሻሽለው መምጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።