በአስራ ስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት አራተኛ የጨዋታ ቀን የሚከናወኑ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከባህር ዳር ከተማ
የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር በሰንጠረዡ ሁለት ፅንፎች የሚገኙትን ኢትዮ ኤሌክትሪኮችን ከባህር ዳር ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።
ከዓመታት ቆይታ በኃላ በተመለሱበት የፕሪምየር ሊግ ውድድር ተፎካካሪ ለመሆን እየተቸገሩ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመሪያው ዙር አንድ ጨዋታን ብቻ አሸንፈው በአጠቃላይ በስምንት ነጥቦች ከሊጉ ግርጌ በአንድ ደረጃ ከፍ ብለው በአስራ አምስተኝነት አጠናቀዋል።
ከዘጠነኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ቡድናቸው ውጤቶችን በሰንጠረዡ ለማስመዝገብ ይቸገር እንጂ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አሁንም የሚያስከፋ ያለመሆኑ ነገር ወደ ሁለተኛው ዙር ሲያመሩ ተስፋ እንዲሰንቁ የሚያደርጋቸው እውነታ ነው።
ወደ ውጤታማነት ለመምጣት በማለም ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉ ሲሆን እነዚሁ በንፅፅር የተሻለ ልምድ ያላቸው አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ከቡድኑ ጋር በምን ያህል ፍጥነት ተዋህደው የቡድኑን በሊጉ የመቆየትን ውጥን ያሳካሉ የሚለው ጉዳይ ከነገ ጀምሮ መታየት ይጀምራል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በነገው ጨዋታ የኢብራሂም ከድርን አገልግሎት የማግኘታቸው ነገር ሲያጠራጥር የተቀረው ስብስብ ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ዝቅተኛ ሽንፈት(2) ያስተናገዱት ባህር ዳር ከተማዎች አስደናቂ አጀማመር ቢያደርጉም በመጀመሪያ ዙር ካደረጓቸው የመጨረሻ ስድስት መርሃግብሮች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች ሰባቱን ብቻ በማሳካት የመጀመሪያውን ዙር ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በስምንት ነጥቦች ርቀው በሃያ ሰባት ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በፈጣን የመስመር ተጫዋቾቻቸው ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አማራጭን ተግባራዊ የሚያደርጉት ባህር ዳሮች በሁለተኛው ዙር ይበልጥ በሰንጠረዡ አናት ተፅዕኖ ለመፍጠር ማጥቃታቸው ተለዋዋጭ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተያያዘም ሁነኛ የፊት አጥቂያቸውን ከሳምንታት በፊት በስነ ምግባር ችግር መቀነሳቸውን ተከትሎ የአማራጭ እጥረት ይገጥማቸዋል ተብሎ ቢገመትም ባለፉት ቀናት ግን ክለብ አልባ ሆኖ የቆየውን የቀድሞ አጥቂያቸው ማሊያዊውን ማማዱ ሲዲቤን ወደ ቡድናቸው መቀላቀል የቻሉ ሲሆን ተጫዋቹ ከአዲሱ ቡድኑ ጋር ልምምድ ባለመስራቱ የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን ከሲዲቤ ውጭ ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሌላ ተጫዋች ግን የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ዳር ስታዲየም በተገናኙበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች ከመመራት ተነስተው ሁለት ለአንድ ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሻረው ጌታቸው በረዳት ዳኝነት ፣ ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።
አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ
የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ ደረጃቸውን ለማሻሻል ሙሉ ሦስት ነጥብን አጥብቀው የሚሹትን ሁለቱን ቡድኖች ያፋልማል።
በወጣቱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው ዙር ባደረጓቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች አስራ ስምንት ነጥቦች በመሰብሰብ ዙሩን በአስራ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ሲችሉ በአስገራሚ መልኩ ያስቆጠሩት(18) ሆነ የተቆጠረባቸው(18) ግብ መጠን እኩል ሆኗል።
በተለይ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ ችግሮች የነበሩበት ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ግን በዚህ ረገድ እምርታን እያሳየ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው ዙርም ይህን ሂደት ማስቀጠል የግድ ይላቸዋል።
በብዙ መመዘኛዎች አማካይ የሚባል የመጀመሪያ ዙርን ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች ምንም እንኳን በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ምንም አይነት ተጫዋችን ወደ ስብስባቸው አለመቀላቸው ሆነ በስነ ምግባር ችግር የተቀጡ ነባር ተጫዋቾች ከመኖራቸው ጋር ተዳምሮ በሁለተኛው ዙር የተሻሻለ ጊዜን ለማሳለፍ የሚያልሙ ከሆነ ከተስፋ ቡድኑ ከተገኙ ተጫዋቾች ብዙ የሚጠብቁ ይመስላል።
አዳማ ከተማዎች በስነምግባር ችግር ከስብስቡ የተነጠሉትን ሦስት ተጫዋቾች ጨምሮ ጉዳት ያስተናገደውን አማኑኤል ጎበናን በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።
በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች አንጋፋውን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት የሾሙት ፋሲል ከነማዎች የመጀመሪያውን ዙር በሃያ አንድ ነጥቦች በሰባተኛ ደረጃ ነበር የቋጩት።
ከአሰልጣኝ ለውጥ በኃላ መነቃቃት ላይ የሚገኘው ቡድኑ በአሰልጣኙ የመጀመሪያ ይፋዊ ጨዋታ ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ በኃላ ከድል ሲታረቁ በሁለተኛ ጨዋታቸው ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከብርቱ ፉክክር ጋር ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ባልተጠበቀ መልኩ በጥቅሉ ደካማ ጊዜያትን ያሳለፉት ፋሲሎች በተለይ በማጥቃቱ ረገድ የነበራቸው አፈፃፀም ፋሲልን የሚመጥን አልነበረም።ዓምና ከአስራ አምስት ጨዋታዎች በኃላ ሃያ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ የነበረው ቡድኑ ዘንድሮ ይህ ቁጥር በአስር የመቀነሱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነበር።
ታድያ ፋሲሎች በሁለተኛው ዙር ተሻሽለው ለመቅረብ በተለይ በግለሰቦች የአቋም መውረድ ሆነ የተጫዋቾች ጥራት ችግር ብዙ ውስንነቶች የነበሩበትን የቡድኑን ማጥቃት ለማሻሻል ለማጥቃቱ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩትን ፈጣኑን ዱላ ሙላቱን እና ሁለገቡን ኦሲ ማውሊን ወደ ስብስባቸው የቀላቀሉ ሲሆን ሁለቱ ተጫዋቾች ከነገ ጀምሮ ለአዲሱ ክለባቸው ግልጋሎትን የሚሰጡ ይሆናል።
በፋሲሎች በኩል አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ በጉዳት ምክንያት እንዲሁም ተከላካዩ መናፍ ዐወል ደግሞ በአምስት ቢጫ የነገው ጨዋታ የሚያመልጣቸው ይሆናል።
በሁለቱ ቡድኖች የመጨረሻ በነበረው የሊጉ ግንኙነታቸው ፋሲል ከነማዎች 2-1 መርታታቸው የሚታወስ ሲሆን በጥቅሉ በሊጉ ባደረጓቸው አስራ ሦስት ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች አምስቱን በመርታት የበላይነት ሲይዙ አዳማዎች በአንፃሩ ሁለት ጨዋታዎችን ሲረቱ የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ።
የምሽቱን ጨዋታ ተፈሪ አለባቸው በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አበራ አብርደው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ረዳቶች ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ አራተኛ ዳኛ በመሆን እንደሚመሩት ይጠበቃል።