ሪፖርት| ዮሴፍ ታረቀኝ አሳዳጊ ክለቡን ታደጓል

አዳማ ከተማ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ፋሲል ከነማን ከመመራት ተነስቶ 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

አዳማ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት ወልቂጤን ካሸነፈው ስብስብ አቡበከር ወንድሙን በሚልዮን ሰለሞን ቀይረው ሲገቡ ዐፄዎቹ በበኩላቸው ሱራፌል ዳኛቸው በበዛብህ መለዮ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ባደረጉበት አጋማሽ ብዙ ሙከራዎች ያልታዩበት እና በተደጋጋሚ ጥፋቶች የታጀበ ነበር። በሙከራ ደረጃ ቀዳሚ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ነበሩ። አምሳሉ ጥላሁን ከመስመር የተሻማውን ኳስ ለማውጣት ባደረገው ጥረት የግብ ጠባቂው ጥረት ባይታከልነት ኳሱ ተጨርፎ ወደ ራሱ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።

\"\"

ብዙም ሳይቆይም በአዳማ ሳጥን ውስጥ ጥፋት በመሰራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጤት ምት አምበሉ አስቻለው ታመነ መትቶ ሳይጠቀምነት ቀርቷል። በሂደቱም የአዳማው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ ያሳየው ብቃት አስደናቂ ነበር። ከዚህ በኋላ በሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩት አዳማዎች በአቡበከር ወንድሙ እና ደስታ ዮሐንስ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ደስታ ከቅጣት ምት በቀጥታ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። በአጋማሹ ከተሻለው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ውጭ ወደ ተጋጣሚ ተጠግተው ዕድሎች መፍጠር የተቸገሩት ዐፄዎቹ በሽመክት ጉግሳ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ወርቃማ ዕድል ካባከኑ በኋላ በ30ኛው ደቂቃ በታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት ግሩም የቅጣት ምት ግብ አስቆጥረዋል።

ጥራት ያለው ሙከራ ባልታየበት አጋማሽ የመጨረሻው ሙከራ የነበረውም አቡበከር ከመስመር የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያመከነው ወርቃማ ዕድል ነበር። አስራ ሥስት ጥፋቶች የተሰሩበት እና በተደጋጋሚ ፊሽካዎሽ እየተቆራረጠ የተካሄደው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ሁለት ተጫዋቾች በጉዳት ተቀይረው ወጥተዋል።

የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገውን ኦሴይ ማውሊ ሽመክት ጉግሳ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ በርካታ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እና ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ያልተደረጉበት ነበር።

\"\"

ሆኖም በዐፄዎቹ በኩል ታፈሰ ሰለሞን ከሳጥን ውጭ መትቶ ሰይድ የመለሰበት እና በአዳማዎች በኩልም በሁለት አጋጣሚዎች ከቆመ ኳስ ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

በ81ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ታረቀኝ ደስታ ዮሐንስ ከርቀት ያሻገረውን እና ቢኒያም አይተን ያወረደውን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው በላይ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላም የዐፄዎቹ ተጫዋቾች የአርቢትሩ ፊሽካ ኳሱ ከመቆጠሩ አስቀድሞ በመስማቱ በግቡ ተገቢነት ላይ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ንትርክ ውስጥ ሲገቡ ታይተዋል። በዚህ መሀልም በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው የዕለቱ ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

ጨዋታው ዳግም ሲቀጥል ፋሲሎች ወደ ቀደመ መረጋጋታቸው መመለስ ሳይችሉ ሲቀሩ በእንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት አዳማዎች በተጨማሪ ደቂቃ በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከቅጣት ምት የተደረገው ሙከራም አግሚውን ታኮ ወደ ውጪ ወጥቷል። 95ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ዮሴፍ ታረቀኝ ግብ አስቆጥሮ አዳማ ከተማን ታድጓል። ጎሉ እንደ መጀመርያው ግብ በተመሳሳይ ከደስታ ዮሐንስ እግር ተነስቶ ወደ ግብነት የተቀየረ ኳስ ነው።

ጨዋታው ከመጠናቀቁ ከጥቂት ሴኮንዶች በፊትም ፋሲል ከነማዎች በናትናኤል አማካኝነት አስቆጪ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው በአዳማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ቀድመው ሀሳባቸው የሰጡት የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጎሉ ለማስጠበቅ አፈግፍገው እንዳልተጫወቱ ከገለፁ በኋላ ከግቡ በኋላ ስለታየው ሥነምግባር \”ተጫዋቾቹ ምክንያት አላቸው የዳኛው ውሳኔዎች ስሜታዊ ያደርጋሉ\” ብለው ተጫዋቾቻቸውን ተከላክለዋል። በመጨረሻም \”በፋሲል ከነማ ቤት የውጤት ቀውስ ተቀባይነት የለውም እኛም ውጤቱን ለማስተካከል እንሰራለን።\” ብለዋል።

ቀጥለው ሀሳባቸው የሰጡት የአዳማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በጨዋታው ውጤት ደስ እንደተሰኙ ገልፀው \”በሁለተኛው አጋማሽ የፈጠርነው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጎሉን እንድናገኝ ረድቶናል\” ብለዋል። አሰልጣኙ ቀጥለውም ወጣት ተጫዋቾችን አወድሰዋል። \”የተጫዋቾቼ ፍላጎት እንድናሸንፍ ረድቶናል ፤ በወጣቶቹ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ ግን ገና እየጀመሩ ነው የመጫወት ፍላጎታቸውም ደስ ብሎኛል\” ብለዋል። በስተመጨረሻም \”በጣም ውድ ሦስት ነጥብ ነው ያገኘነው\” ብለው የድሉን ታላቅነት ገልፀዋል።