የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሣምንት ዛሬ ሲጀመር ሀዋሳ ከተማ ፣ መቻል እና ይርጋጨፌ ቡና ድል ቀንቷቸዋል።
ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ 0-3 ሀዋሳ ከተማ
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ሀዋሳዎች ብልጫ በወሰዱበት የመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። 25ኛው ደቂቃ ላይም ሲሣይ ገ/ዋህድ በግሩም ዕይታ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው እሙሽ ዳንኤል የግብ ጠባቂዋን መውጣት በመመልከት እና ከፍ አድርጋ በመምታት ነጥሮ መረቡ ላይ እንዲያርፍ አስችላለች። መሀል ሜዳው ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ንፋስ ስልኮች እየተረጋጉ እና እየተደራጁ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓትም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። 40ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ ከቀኝ መስመር ለእሙሽ ዳንኤል ለማቀበል በሚመስል መልኩ ያሻገረችው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ግብ ሆኗል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የንፋስ ስልኳ ሳሮን ሰመረ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሞክራው በቀኙ ቋሚ በኩል የወጣው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንጻር በእንቅስቃሴ ረገድ እየተዳከሙ ይምጡ እንጂ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ኃይቆቹ ሁለት ንፁህ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ በቅድሚያም 71ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ ሳጥን ውስጥ ከግብ ጠባቂዋ ከፍ አድርጋ የሞከረችው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት 77ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ክለቧን የ3-0 ባለድል አድርጋለች።
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 መቻል
08:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጪ አንድ የግብ ዕድል ብቻ የተፈጠረበት ነበር። 36ኛው ደቂቃ ላይ የመቻሏ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ የጊዮርጊስ ተከላካዮች በተዘናጉበት ቅጽበት ባገኘችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን በእግሯ መልሳባታለች።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ለተመልካች አሰልቺ ሆኖ ሲቀጥል 69ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ከቅጣት ምት ያደረገችውና ግብ ጠባቂዋ በረከት በእግሯ የመለሰችባት ሙከራ በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ነበር። በየጨዋታዎቹ ላይ ካላቸው ማራኪ የኳስ ቅብብል በኋላ ሙሉ ደቂቃ በተመሳሳይ ብርታት ለመጨረስ ሲቸገሩ የሚታዩት እንስት ፈረሰኞች 90ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። ገነት ኃይሉ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት መትታ ባስቆጠረችው ግብም መቻልን የ1-0 ጣፋጭ ድል ባለቤት አድርጋለች።
ልደታ ክ/ከ 0-1 ይርጋጨፌ ቡና
በዛሬው የመጨረሻ ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ 22ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ ትርሲት መገርሣ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ከቆሙት ተጫዋቾች ሁሉ በቁመት የምታንሰው ዳግማዊት ሰለሞን በግሩም ዕይታ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራው ይርጋጨፌን መሪ አድርጋለች።
ከመኃል ሜዳ ሳይረጋጉ በቶሎ የሚነሱ ኳሶችን በመጠቀም በማጥቂያ መስመሮች ብልጫውን ለመውሰድ ብርቱ ፍልሚያ የተደረገበት ጨዋታ የግብ ዕድሎች ግን እንደ ቀደመው ጨዋታ ሁሉ ያልተፈጠሩበት ነበር። ጨዋታውም በይርጋጨፌ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።