በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን እንደሚከተለው መርጠናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ
አዳማ ከተማ ወሳኝ ድልን ሲያሳካ የግቡ ዘቡ ሚና ቀላል አልነበረም። በጨዋታው በፋሲል ከነማ ተደጋጋሚ ሙከራ ቡድኑ ቢያስተናግድም ግብ ጠባቂው ከታፈሰ የቅጣት ምት ጎል ውጪ ሌሎች ጥቃቶችን ሲመክት የነበረበት መንገድ አስገራሚ የነበረ ከመሆኑ በዘለለ የመጨረሻዋን የናትናኤል የቅጣት ምት ኳስ በማዳን ክለቡን የታደገበት ወሳኝ ቅፅበት በምርጥነት አስመርጦታል።
ተከላካዮች
ግሩም ሀጎስ – መቻል
መቻል ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የ 2-1 ድል ሲቀዳጅ በጉዳት ከአንድ ጨዋታ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው የመስመር ተከላካዩ የተሳካ ቀን አሳልፏል። በተለይም ከነዓን ማርክነህ ላስቆጠረው የመጀመሪያ ግብ በተዘዋዋሪ መንገድ ቁልፍ መነሻ ሲሆን በመከላከሉ እና በማጥቃቱ ያሳየው ጠንካራ እንቅስቃሴ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።
ፍሪምፓንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተጠባቂው ጨዋታ ከመድን ላይ ሦስት ነጥብ ሲሸምቱ የጋናዊው የመሀል ተከላካይ ፍሪምፓንግ ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ምንም እንኳን ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉ ደካማ ሆኖ ቢቀርብም በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ወጥነት ሲታይበት የተከላካዩ አሰተዋጽኦ የላቀ ከመሆኑ ባለፈ ቡድኑ ሲመራ በነበረበት ወቅት የአቻነት ጎል ከማይመች ቦታ ማስቆጠሩ በሳምንቱ ምርጥ ስብስባችን ውስጥ ልናካተው ችለናል።
በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ
በኃይቆቹ መለያ 929 ደቂቃ ያሳለፈው በረከት ቡድኑ ለገጣፎ ለገዳዲን ሲረታ ወሳኙዋን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል። ተጫዋቹ በጨዋታው በተለይ ከቆሙ ኳሶች ያልተጠበቀ የጎል ምንጭ ከመሆንም ባለፈ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ የነበሩትን ለገጣፎዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ለመመከት ሲጥር ነበር ፤ አጠቃላይ የመከላከል ውቅሩንም ሲመራ የነበረበት መንገድ የመሐል ተከላካይ ነጥሮ ባልታየበት የጨዋታ ሳምንት እንዲመረጥ አድርጎታል።
ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ
አዳማ ከተማ ሲመራ ከነበረበት የፋሲሉ ጨዋታ አንሰራርቶ ድልን ሲጎናፀፍ የግራ መስመር ተከላካዩ አስደናቂ እንቅስቃሴ አብሮ ይነሳል። ከተፈጥሯዊው ቦታው ወደ ፊት ተስቦ ሲጫወት የነበረው ተጫዋቹ አዳማ ከተማ ወደ ጨዋታ ተመልሶ በዮሴፍ ታረቀኝ ሁለት ግቦች አሸንፎ ሲወጣ ባለግራ እግሩ ሁለቱንም ወደ ግብነት የተለወጡ ኳሶችን በማቀበሉ የምርጥ ስብስባችን አካል አድርገነዋል።
አማካዮች
ሔኖክ ሀሰን – ድሬዳዋ ከተማ
በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገድ ጫና ውስጥ የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን በመርታት እፎይታ ባገኙበት ጨዋታ ሔኖክ ሀሰን ቦታው የሚፈልገውን ሚና ከመወጣቱ ባለፈ ታክቲካል ዲሲፒሊን በመሆን የተቃራኒ ቡድን እንቅስቃሴ የማቋረጥ ስራዎቹን በአግባቡ በመከወን እና የተመጠኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ የማቀበል ሚናው የጎላ የነበረ በመሆኑ በኮከብነት ምርጫ ውስጥ ሊካተት ችሏል።
ከነዓን ማርክነህ – መቻል
እንደ ሌላኛው የቡድን አጋሩ ግሩም ሀጎስ መቻል ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ድል ሲያደርግ የተሳካ ቀን ያሳለፈው ከነዓን በተለይም በዝናብ ምክንያት ጭቃ ሆኖ የተበላሸው ሜዳ በሚፈልገው ኃይል እጅግ አስደናቂ በሆነ ብርታት ለበርካታ ደቂቃዎች ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ሲያደርግ በስሙም አንድ ግብ አስመዝግቧል።
ፉዐድ ፈረጃ – ባህር ዳር ከተማ
ባህርዳር ከተማ በኤሌክትሪኩ ፍልሚያ ቅድሚያ ግብ ቢቆጠርበትም ያገኘውን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ በመጠቀም በተለይም መኃል ሜዳው ላይ በእጅጉ ተሻሽሎ ብልጫ ሲወስድ የፉዓድ ፈረጃ ብቃት አስደናቂ ነበር። ተጫዋቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ባያደርግም ከዕረፍት መልስ ግን የአቻነት ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ወደ ጨዋታው በመመለስ ሲያነቃቃ በጋለ የጨዋታ ስሜት ያሳለፋቸው የመጨረሻ ደቂቃ ትዕይንቶችም በቦታው ተመራጭ አድርገውታል።
አጥቂዎች
ተመስገን ደረሰ – አርባምንጭ ከተማ
የአርባምንጭ ከተማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ተመስገን ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ግብ ባያስቆጥርም የቡድን አጋሮቹ ያስቆጠሩትን ጎል አመቻችቶ አቀብሏል። አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈም በግሉ የግብ ምንጭ ለመሆን የጣረበት መንገድ እንዲሁም በመከላለሉ ረገድ ወደ ኋላ እየተመለሰ ያደረገው አበርክቶ ድንቅ ነበር።
ሀብታሙ ታደሠ – ባህር ዳር ከተማ
ባህርዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ኤሌክትሪክን 3-1 ሲረታ ተጋጣሚው ላይ ያገኘው የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ትልቅ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ቡድኑ እንዲያሸንፍ የመጨረሻ ደቂቃ ግቦች ያስፈልጉት ነበር። ሁለቱን የመጨረሻ ግቦች በስሙ ያስመዘገው ሀብታሙ ታደሠ ደግሞ ከውጤታማነቱ አንጻር ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ ሆኗል።
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
በቅርብ የሊጉ ሳምንታት ላይ እያስደመሙ ካሉ ወጣቶች መካከል ከፊት የሚሰለፈው የመስመር አጥቂው ዮሴፍ ታረቀኝ የታችኛው የአዳማ ቡድን ፍሬ ሲሆን ቡድኑ ፋሲልን 2ለ1 በረታበት ጨዋታም ሁለት ያገኛቸውን ኳሶች በአግባቡ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን በድል ማንበሽበሽ መቻሉ በምርጥነት በስብስባችን አካተዋል።
አሠልጣኝ
ፋሲል ተካልኝ – መቻል
ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደውን መቻል የሚመሩት አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ድል ያስመዘገበበትን ውጤት እንዲያገኝ ያስቻሉበት መንገድ ድንቅ ነበር። በፈታኙ የጭቃ ጨዋታም ጠንካራውን ሀዲያ ሆሳዕና ገጥመው የቡድኑን ጠንካራ ጎን በማሳነስ ለሜዳው እና ለተጋጣሚያቸው የሚሆን ፈጣን አጨዋወት በመከተል ጨዋታውን በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ገድለው ቀሪውን ደቂቃ የተቆጣጠሩበት መንገድ የምርጥ ቡድናችን ተመራጭ አሠልጣኝ አድርጓቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ፍሬው ጌታሁን
ሚሊዮን ሰለሞን
ምንተስኖት አዳነ
አብዱልከሪም ወርቁ
ያሬድ ታደሰ
ኤሊያስ አህመድ
ኪቲካ ጅማ
እስማኤል ኦሮ-አጎሮ