የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።
ቦሌ ክ/ከ 1-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ለተመልካች ሳቢ በነበረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቦሌዎች እጅግ አስደናቂ አጀማመር ማድረግ ችለው ነበር። 7ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ ትርሲት ወንደሰን ከረጅም ርቀት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ስታስወጣባት ያ ኳስም ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ተሻምቶ ከሁለት ንክኪዎች በኋላ ያገኘችው ስንታየሁ ኢርኮ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር ቦሌን መሪ አድርጋለች። በማራኪ የኳስ ቅብብል የተመልካቹን ትኩረት የሳቡት ቦሌዎች ቀስ በቀስ ግን ከጨዋታ ግለታቸው እየቀዘቀዙ ሄደዋል። መኋል ሜዳው ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ንግድ ባንኮችም 31ኛው ደቂቃ ላይ ሰናይት ቦጋለን ቀይረው በማስገባት ጨዋታውን መቆጣጠር እና 35ኛው ደቂቃ ላይም በሎዛ አበራ ግብ አቻ መሆን ሲችሉ ወደ ዕረፍት ሊያመሩ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥም ሎዛ አበራ ለራሷ እና ለቡድኗ ሁለተኛ ግብ አስቆጥራ ንግድ ባንክ አጋማሹን መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ዕረፍት ላይ ተቀይራ የገባችው የባንኳ ኝቦኝ የን 47ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጋ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት በሰኮንዶች ልዩነት ቦሌዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ምርጥነሽ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ባሻገረችላት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘችው የቀደመውን የአጨራረስ ብቃቷን ለማግኘት የተቸገረችው ንግሥት በቀለ ሳትጠቀምበት ቀርታ ትልቅ የግብ ዕድል አባክናለች። ከዚህ እንቅስቃሴ በኋላ ግን ንግድ ባንኮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ጨዋታውን ሲቆጣጠሩ 50ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከግራ መስመር ያደረግቸውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስትመልስባት ኳሱን ያገኘችው ሎዛ አበራ ያደረገችው ሙከራም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶባታል።
አልፎ አልፎ በሚያሳዩት ማራኪ የኳስ ቅብብል ከተመልካቾች አድናቆት ያልተለያቸው ቦሌዎችም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ሲቸገሩ 74ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አረጋሽ ካልሳ በግራ መስመር ገፍታ የወሰደችውን ኳስ አክርራ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አርባምንጭ ከተማ 3-0 አዲስአበባ ከተማ
08፡00 ሲል በጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አርባምንጮች ብልጫውን ሲወስዱ 12ኛው ደቂቃ ላይም ቤተልሔም ሰማን ከሳጥን ውጪ ግሩም ግብ አስቆጥራ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ግን አዲስ አበባዎች በተሻለ የጨዋታ ሂደት በጨዋታው ብልጫውን እየወሰዱ መጥተዋል። በተለይም 32ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ረሒማ ዘርጋው በግንባሯ በመግጨት አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ንግሥት ኃይሉ ወደ ግብ እርግጠኛ ሆና የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሔም ዮሐንስ በግሩም ንቃት መልሳባት ትልቁን የግብ ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ አርባምንጮች ከጨዋታ ውጪ የሆነ ግብ አስቆጥረው ነበር። ሆኖም ረዳት ዳኛዋ ሱላማጢስ ኪሮስ እና ዋና ዳኛዋ አዲስዓለም ቢሻው ባለመተያየታቸው ግቡ ፀድቆ አርባምንጮች ደስታቸውን መግለፅ ሲጀምሩ ለጥቂት ሴኮንዶች ዘግይታ የረዳቷን ምልክት ያየችው ዋና ዳኛዋ ግቡን ሽራዋለች። በዚህ አጋጣሚ በአርባምንጮች በኩል ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦ ክስ ተመዝግቧል። ጨዋታ አቋርጦ ክስ የማስመዝገብ ሂደትም የሊጉን ደረጃ እጅግ የሚያወርድ እና ለተመልካችም እጅግ አሰልቺ በመሆኑ በቶሎ ሊቀረፍ ይገባዋል።
በጨዋታው በተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት አርባምንጮች 58ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ቤተልሔም ሰማን ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ሠርካለም ባሳ በግንባሯ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። 81ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይራ የገባችው ቤተልሔም ታምሩ ተከላካዮችን አታልላ በማለፍ በግሩም አጨራረስ ሦስተኛ ግብ አስቆጥራለች።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አዲስ አበባዎች ተጭነው ሲጫወቱ 84ኛው ደቂቃ ላይ ረሒማ ዘርጋው ከግብ ጠባቂ ጋር ብትገናኝም ሳትጠቀምበት ስትቀር 88ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ ከሳጥን ውጪ የዓየር ላይ ኳስ ሞክራ በግብ ጠባቂዋ እና በግቡ አግዳሚ ተመልሶባታል። ሆኖም ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ 0-0 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ
የሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር አዳማ ከተማን ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማን ሲያገናኝ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የተሻለው ሙከራ 5ኛው ደቂቃ ላይ ተደርጓል። የአዳማዋ ግብ ጠባቂ መሠረት ባጫ ከሳጥን ውጪ ኳስ በእጇ በመንካቷ የተሰጠውን የቅጣት ምት ዓለም በዬቻ በጥሩ ሁኔታ ብትሞክረውም ራሷ ግብ ጠባቂዋ መሠረት ባጫ መልሳባታለች።
ከተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት አዳማዎች የሜዳው ሦስተኛ ክፍል ላይ ግን የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዳይሆኑ ሲያደርጋቸው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ንፋስ ስልኮችም 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቅድስት ባደግ ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ሳሮን ሰመረ ሳታገኘው ቀርታ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። በአጋማሹ የተሻለው የግብ ዕድልም 92ኛው ደቂቃ ላይ በንፋስ ስልኮች ሲፈጠር በሬዱ በቀለ በግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ወደ ውስጥ ስታሻግረው ሔርሜላ ይገዙ ሳታገኘው ቀርታ የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።