በምሽቱ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን 1-0 በማሸነፍ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።
ከጅምሩ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ላይ ያመዘነው ጨዋታ አደገኛ የግብ ዕድሎች እንደልብ የተፈጠሩበት አልነበረም። ቡድኖቹ ከአማካይ ክፍሎቻቸው የኳስ ቁጥጥር መነሻነት ጥቃቶችን የመሰንዘር ዕቅድ ያላቸው ቢመስልም ለአጥቂዎቻቸው ንፁህ ዕድል መፍጠሩ ላይ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። በእርግጥ የቅብብሎቻቸውን መዳረሻ በቀኝ መስመር በተደጋጋሚ በሚታየው የአማኑኤል እንዳለ ቀጥተኛ ሩጫዎች ላይ ያደረጉት ሲዳማዎች በንፅፅር ወደተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ የተሻሉ ነበሩ።
በኋላ ክፍላቸው ላይ በርከት ያሉ ለውጦችን በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩት ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ባሰቡት ልክ በቅብብል ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ለመድረስ ቢቸገሩም 31ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ አስቆጥረዋል። ግማሽ ጨረቃው አካባቢ በፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ በማራኪ ሁኔታ በመምታት ከመረብ አገናኝቶታል።
በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎችም ነብሮቹ ጨዋታው በክፍት እንቅስቃሴ እና በማዕዘን ምቶች በተጋጣሚ ሜዳ ላይ እንዲያመዝን ማድረግ ችለው በመሪነት ጨርሰዋል።
ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾች ቅያሪ እና የሚና ሽግሽግ ያደረጉት ሲዳማዎች በጥሩ የማጥቃት ጫና ጀምረዋል። ሁለቱ ተቀያሪዎች በተጣመሩበት ሙከራም 49ኛው ደቂቃ ላይ ፍሊፕ አጃ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያሳለፈውን ይስሀቅ ካኖ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የሲዳማዎች የእንቅስቃሴ የበላይነት ቀጥሎ 67ኛው ደቂቃ ላይም ፍሊፕ አጃ ከሳላዲን ሰዒድ የግንባር ኳስ ከግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ሙከራውን ያሬድ አድኖበታል።
የተጋጣሚያቸውን ጫና ለማርገብ ወደራሳቸው ሜዳ የተሳቡት ነብሮቹ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች እንዳይፈጠሩ በማድረጉ ቢሳካላቸውም የማጥቃት ምልክቶችን ያሳዩት ጨዋታው ከ70ኛው ደቂቃ ከተሻገረ በኋላ ነበር። ይህም በቡድኖቹ መካከል የተሻለ የማጥቃት ምልልስ እንዲታይ ያደረገ ነበር።
ሆኖም ጥድፊያ የበዛበት የሲዳማ ጥቃት አልፎ አልፎ ከሳጥን ውጪ በተደረጉ ሙከራዎች ሲገደብ ሆሳዕናዎችም ስኬታማ የማጥቃት ሽግግር አድርገው ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በ1-0 ውጤት ሊፈፀም ችሏል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በሰጡት አስተያየት የጨዋታውን ክብደት አንስተው ውጤት በማስጠበቁ እንደተሳካላቸው እና የአጨራረስ ችግራቸው ግን አሁንም መስተካከል እንደሚገባው አስረድተዋል። አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በበኩላቸው በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀሳቸውን አንስተው የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አስገብተው ጎል ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ብዙ መስራት እንዳለባቸው አንስተው አዲስ ፈራሚዎቻቸው ደስታ ደሙ እና ፍሊፕ አጃ ያሳዩት አጀማመር ጥሩ መሆኑን አስረድተዋል።