በምሽቱ ጨዋታ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 በመርታት ከተከታዮቹ ያለውን ርቀት አስፍቷል።
በቁጥር አነስተኛ የግብ ሙከራዎች ባስተናገደው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚው አጋማሽ አዘንብሎ ተንቀሳቅሷል። ከኳስ ውጪ በሜዳቸው ላይ ክፍተቶችን በመዝጋት ጥሩ አደረጃጀት የነበራቸው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 8ኛው ደቂቃ ላይ በኢብራሂም ከድር የቅጣት ምት ሙከራ ያድርጉ እንጂ በማጥቃት ወቅት በቁጥር አንሰው በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ይደርሱ የነበረበት ደካማ የማጥቃት ሽግግር ሂደት ዕድሎችን ከመፍጠር አግዷቸዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በእንቅስቃሴ የተሻሉ ይሁኑ እንጂ የግብ አጋጣሚዎችን በብዛት አልፈጠሩም። 10ኛው ደቂቃ ላይ ልደቱ ለማ በግንባሩ ኳስ ለማውጣት ብሎ በራሱ ላይ ሊያስቆጥር የነበረበትን አጋጣሚ ካክፖ ቼሪፍዳይን ካዳነ በኋላ ናትናኤል ዘለቀ በ21ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር እንዲሁም 31ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ራሱ ናትናኤል አቤል ያለው ሳጥን ውስጥ ያመቻቸለትን ኳስ የሞከረባቸው የግብ አጋጣሚዎች ብቻ ተፈጥረዋል።
ጨዋታው በአመዛኙ በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ተገድቦ ሲቀጥል ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን ሲያገኙ የቆዩት ፈረሰኞቹ ከዚሁ ምንጭ ጎል አግኝተዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ሄኖክ አዱኛ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ግብ አድርጎታል።
ከግቡ በኋላም 44ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም ከጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ብቻ ትኩረት ሳቢ ሆኖ ጨዋታው ተጋምሷል።
ሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ በጊዮርጊሶች የእንቅስቃሴ የበላይነት ቢቀጥልም ሙከራ የተመለከትነው ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣ ቸርነት ጉግሳም የጎን መረብ ላይ ያረፈበትን ሁለት ተከታታይ ሙከራዎች በሰከንዶች ልዩነት አድርገዋል።
በመቀጠል 70ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ያለው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በግንባሩ ማድረግ ችሏል። ፊት መስመር ላይ ለውጥ ቢያደርጉም የማጥቃት አቅማቸው ያልተሻሻለው ኤሌክትሪኮች የጨዋታውን የተሻለ ሁለተኛ ሙከራቸውን 72ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየው ዋለጬ ከሳጥን ውጪ መትቶት ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ ማድረግ ችለዋል።
በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይበልጥ ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ጋቶች ፓኖም ወደ ውጪ የወጣበትን ፣ ቢኒያም በላይ በግቡ ቋሚ የተመለሰበትን ፣ ረመዳን የሱፍ ደግሞ በግብ ጠባቂ የዳነበት ሙከራዎች በጊዮርጊስ በኩል ታይተዋል። ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃ ካመራ በኋላም ነፃነት ገብረመድህን በቢኒያም በላይ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሸረፋ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል። ጨዋታውም በፈረሰኞቹ 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በጨዋታው ከዚህ በላይ ጎል ማግባት ይችሉ እንደነበር በማንሳት ተጋጣሚያቸው ቀላል እንዳልነበር ጠቁመው አጥቂያቸው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በጤንነቱ ከቀጠለ የአቡበከር ናስርን ሪከርድ ሊሰብር እንደሚችል ሀሳባቸውን ገልፀዋል። አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጫዋቾቻቸው በፈለጉት መንገድ አለመንቀሳቀሳቸውን አስረድተው ፊት መስመር ላይ ቡድናቸው ያለበትን ችግር የጠቆሙ ሲሆን አዲስ ፈራሚዎቻቸው ጥሩ እንደተንቀሳቀሱ ተናግረዋል።