ከነገው ጨዋታ በፊት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ምን አሉ ?

👉\”ጥሩ መንፈስ ላይ ስለሆነ ያለነው ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለው\”

👉\”እነሱን ማወቁ የሚጠቅምህ ነገር አለ ፤ ግን ለጨዋታው የምታደርገው ዝግጅት እና በዕለቱ ይዘከው የምትቀርበው ነገር ነው ውጤቱን የሚወስነው\”


👉\”ተጋጣሚያችንን እናከብራለን ፤ ጨዋታዎቹን ደግሞ እንደ ሞት ሽረት ፍልሚያ እናከናውናቸዋለን\”

ስለዝግጅት ጊዜያቸው…

ጥሪ ካደረግንላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል አንዳንዶቹ አዳዲሶች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው። እነዚህን ተጫዋቾች ይዘን አዲስ አበባ ላይ ዝግጅታችንን ጀምረናል። ከዝግጅት ባለፈም ከሩዋንዳ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገናል። እንደሚታወቀው ግብፅን የገጠመው ብድን ውስጥ የነበሩ አሁን ግን በጉዳት ስብስባችን ውስጥ የሌሉ ተጫዋቾች አሉ። እነ አማኑኤል፣ ዳዋ፣ አስራት እና አቡበከር የመሳሰሉት አሁን የሉም። ከዝናብ ጋር በተያያዘም የልምምድ የሜዳ ችግር ነበረብን። ደስ የሚለው ነገር ግን ተክተን የጠራናቸው ተጫዋቾችም ሆነ ነባሮቹ ተጫዋቾች እያሳዩ ያሉት ተነሳሽነት ትልቅ ነው። በሩዋንዳውም ጨዋታ ያየነው ነገር ጥሩ ነገር ነው። አሁን ላይ ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው።

\"\"

ስለጉዞአቸው…

ከአዲስ አበባ ካዛብላንካ ረጅም ጉዞ ነው ያደረግነው። ለተጫዋቾቻችንም አድካሚ ነበር። ከ24 ሰዓታት በላይ በጉዞ ነው ያሳለፍነው። ሞሮኮ ከገባን በኋላም አንድ የልምምድ መርሐ-ግብር ብቻ ነው ያከናወነው። በዚሁ ጉዞ ምክንያት አንድ ልምምድም መስራት አልቻልንም። ምንም ቢሆን ምንም ግን ለነገው ጨዋታ በሚገባ ተዘጋጅተናል። ትናንትና ሜዳ ላይ የነበረው ልምምድ ላይ ደግሞ ተጫዋቾቹ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ እንደሆኑ ነው ያየሁት።

ስለተጋጣሚ ቡድን…

የትኛውም ቡድን እንደሚያደርገው ተጋጣሚን የመመልከት ስራ ለመስራት ሞክረናል ፤ ግን ደግሞ በቅርብ ያደረጉትን ጨዋታዎች ማግኘት አልቻልንም። የቀደመ ቡድናቸውን ጨዋታዎች ለማየት ሞክረናል። ምናልባት ግን አፍሪካ ዋንጫ ላይ ከነበራቸው ስብስብ የተወሰኑ ተጫዋቾችን እንደቀየሩ አስተውለናል። ዞሮ ዞሮ እነሱን ማወቁ የሚጠቅምህ ነገር አለ ፤ ግን ለጨዋታው የምታደርገው ዝግጅት እና በዕለቱ ይዘከው የምትቀርበው ነገር ነው ውጤቱን የሚወስነው። ጥሩ መንፈስ ላይ ስለሆነ ያለነው ጥሩ ነገር ይገጥመናል ብዬ አስባለው።

ስለጨዋታው ወሳኝነት…

ምንም ቀላል የጨዋታ የለም። የጊኒ ቡድን ጥሩ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። ጥሩ ስብስብ አላቸው። የነገው እና ቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ በምድቡ ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ቡድኖች ላይ ተፅዕኖ ያለው ወሳኝ ጨዋታ ነው። ምንም እንኳን በምድቡ አናት ላይ ብንገኝም ሁሉም ቡድኖች እኩል ነጥብ ነው ያላቸው። ይህንን ተከትሎ የነገው ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ነው። ተጋጣሚያችንን እናከብራለን ፤ ጨዋታዎቹን ደግሞ እንደ ሞት ሽረት ፍልሚያ እናከናውናቸዋለን።

ወደ 2023 አፍሪካ ዋንጫ ለመግባት የምታስብ ከሆነ ማክሲመም ነጥብ መያዝ ነው ፍላጎትህ ፤ የምታቅደውም እርሱን ለማድረግ ነው። ካልተቻለ ደግሞ ብለህ በቅደም ተከተሉ የምታስቀምጣቸው ነገሮች አሉ። ሁሉም ቡድን እንደሚፈልገው ከዚህ ሁለት ጨዋታ ብንችል 6 ነጥብ ለማሳካት ነው ፍላጎታችን። ይሄ ይሳካል ወይ የሚለውን ሜዳ ላይ የምናየው ነው የሚሆነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ ሌሎች አማራጮችን አስቀምጦ መንቀሳቀስ ከአንድ አሠልጣኝ ወይም ቡድን የሚጠበቅ ነው። እዚህ ስንመጣ ጥሩ የሚጫወት እና ነጥብ መሰብሰብ የሚችል ቡድን እንዳለን ያየነው ነው። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ አሳክተናል። እንደሚታወቀው ደግሞ ሁላችንም ሦስት ነጥብ ነው ያለን። በቀጣይ እዚህ ውስጥ ለመቆየት ደግሞ ያሰብነውን ማሳካት አለብን። መሰናክሎቹ እና አስቸጋሪ ነገሮቹ እንዳሉ ሆነው በደንብ እየተዘጋጀን ነው። ይሄንን ስል ደግሞ በጣም ቀላል ቡድን ነው የምንገጥመው እያልኩ አይደለም። አስቸጋሪ ነገር ሊገጥመን ይችላል። ፍላጎታችን ግን ያ ነው። የመጀመሪያም ፍላጎታችን የአፍሪካ ዋንጫውን መቀላቀል ነው። ለዚህ ደግሞ ነጥ ጥ የግድ መያዝ አለብን። እነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው ስል ለአራታችንም ቡድኖች ነው። ሁሉም አሠልጣኞች ስድስት ነጥብ ለማግኘት እንደሚያስቡ ነው የሚነግሩህ።

\"\"

ስለቡድኑ ወጥነት…

ብሔራዊ ቡድኑ ረጅም ጉዞ ነው እያደረገ የሚገኘው። ወጥ ነው ለማለት የሚያስችል ነገር አለ። የቡድኑ አቀራረብ በወጥነት ጥሩ ነገር ውስጥ እየገባን እደሆነ ያለፉትን ዓመታት እያየን ነው። የምዕራብ እና የሰሜን አፍሪካ ቡድኖችን ስንገጥም የነበረንን ሪከርድ ለማሻሻል እየሞከርን ነው። በማላዊም 2ለ1 እንሸነፍ እንጂ በጨዋታው የነበረን ነገር ከግብፅ ጨዋታ ብዙ የተለየ አልነበረም። በአጠቃላይ ቡድኑ ጥሩ መንፈስ ላይ ነው። በአጠቃላይ ቡድናችን ወጥ ነው ብዬ ነው መናገር የምችለው። ማሸነፍ እና መሸነፍ ቀጭን በሆነ መስመር ስለሆነ የሚለየው እሱን መናገር ይከብዳል። ከመጫወት መንገድ ጋር እና ከመፎካከር ጋር ተያይዞ ቡድኑ ወጥ አይደለም የሚለውን ነገር መቀበል ይከብደኛል።

ከማጥቃት ጋር በተያያዘ…

ከማጥቃት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች በአንድ ጀንበር የሚቀረፍ አይደለም። እንደ ቡድን የምንፈታበትን ነገር እያሰብን ነው እየተዘጋጀን ያለነው። በዚህ ሂደት ጎሉን ማን እንደሚያገባው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የግድ አጥቂዎች ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን አያስፈልግም። ሌሎች ተጫዋቾችም ግብ እንዲያስቆጥሩ የሚያደርግ አጨዋወት ላይ ነው ትኩረት እያደረግን ነው ያለነው። ተፈጥሯዊ ከ20 በላይ የሚያገባ አጥቂ እስከሌለህ ድረስ የጎል ችግሬን እከሌ ይፈታዋል ብሎ መናገር አይቻልም። እንደቡድን ግን ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው ያለነው።