የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሣምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር መቻል እና ሀዋሳ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።
ይርጋጨፌ ቡና 0-2 መቻል
የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ይርጋጨፌ ቡናን ከመቻል አገናኝቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ይርጋጨፌዎች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ መኃል ሜዳው ላይ ብልጫ በመውሰድ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለው ነበር። ቀስ በቀስ ግን መቻሎች በዕለቱ ድንቅ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ወደኋላ እየተሳበች በምታደርገው እንቅስቃሴ የተወሰደባቸውን የመኃል ሜዳ ብልጫ ማስመለስ ችለዋል። የመጀመሪያውን የግብ ዕድልም 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ቤዛዊት ተስፋዬ በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ለሴናፍ ዋቁማ አመቻችታ ስታቀብል ሴናፍ ሳጥን ውስጥ ይዛው በመግባት ያደረግቸውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ምህረት ተሰማ በእግሯ መልሳባታለች። በምታሳየው የግል ክህሎት ከተመልካቾች ከፍተኛ አድናቆት የተቸራት ሴናፍ ዋቁማም 39ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮችን አታልላ በማለፍ በግሩም አጨራረስ ግብ አስቆጥራ መቻል ጨዋታውን እንዲመራ አስችላለች።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ሲቀዛቀዝ የመቻሎች የበላይነት የታየበት ነበር። በአጋማሹ ቀዳሚው ለግብ የቀረበ ሙከራም 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ሴናፍ ዋቁማ ከቅጣት ምት ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት ከአሥር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ማዕድን ሳህሉ በተረጋጋ አጨራረስ ባስቆጠረችው ተጨማሪ ግብ የመቻልን መሪነት አጠናክራለች። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር አልፎ አልፎ ከሚያደርጉት የኳስ ቅብብል ውጪ በጨዋታው እጅግ የተፈተኑት ይርጋጨፌ ቡናዎች 72ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ነጻነት ፀጋዬ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ሴናፍ ዋቁማ ኳስ በአየር ላይ እንዳለ ያደረገችውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስባት ያንኑ ኳስ ያገኘቸው ምርቃት ፈለቀም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታውም በመቻል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ በተቀናጀ ማራኪ የኳስ ቅብብል አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ሀዋሳዎች 6ኛው ደቂቃ ላይ ረድዔት አስረሳኸኝ ከሳጥን አጠገብ በግሩም አጨራረስ በግራ እግሯ ባስቆጠረችው ግብም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተፈተኑት ድሬዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ግለት በመምጣት 26ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ሜላት ደመቀ ከግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገችውን ግሩም ሙከራ ግብጠባቂዋ መስከረም መንግሥቱ እና የግቡ አግዳሚ ግብ ከመሆን አግደውታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 70ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳዎች በኩል ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ቅድስት ቴቃ ከረጅም ርቀት እየገፋች ወስዳ ካደረገችው ሙከራ ውጪም በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ለመውሰድ ከተደረገው መጠነኛ ፉክክር በተለየ የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጠርበት ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቦሌ ክ/ከተማ 1-1 ልደታ ክ/ከተማ
በቦሌ ክ/ከተማ እና በልደታ ክ/ከተማ መካከል በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል አንድ አንድ የጠሩ የግብ ዕድሎች ብቻ ተፈጥረውበታል። በቅድሚያም የቦሌዋ አምበል ትርሲት ወንደሰን በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል ስትመልስባት 26ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የልደታዋ ህድዓት ካሱ ከቀኝ መስመር ከሳጥን አጠገብ ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል ቦሌዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ኢርኮ ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በመብዛት 67ኛው ደቂቃ ላይ በንግሥት በቀለ ከረጅም ርቀት ሙከራ ማድረግ የቻሉት ቦሌዎች 75ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። ጤናዬ ለታሞ እየገፋች በወሰደችው ኳስ ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብጠባቂ ጋር ብትገናኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክነዋለች። ይሄም በቦሌዎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ሲሆን በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም ትርሲት ወንደሰን ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል መልሳባታለች። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ቦሌዎች ጨዋታውን የጨረሱት በመምሰል በተዘናጉበት ቅፅበት ያልታሰበ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ልደታዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ህድዓት ካሱ ባስቆጠረችው ግብም አንድ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።