የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በ11 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሁለቱን ምድቦች የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ሲቀናቸው የምድብ \’ሐ\’ መሪው ሀምበርቾ ዱራሜ ነጥብ ጥሏል።
በዳንኤል መስፍን ፣ ቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ
የጠዋት ጨዋታዎች
አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ከ አዲስ ከተማ ክ/ከ – ምድብ ሀ
ተቀራራቢ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ የለ ጎል ተጠናቋል። በሁለቱም በኩል እምብዛብ የጠራ የጎል ሙከራ ያላስመለከተን ይህ ጨዋታ መሐል ሜዳ ላይ ትርጉም የሌላቸው ንክኪዎች ሲደረጉ ተመልክተናል። በመሐል ሜዳ ላይ የተገደበው የአዲስ ከተማ አጨዋወት ጥራት ያላቸው ኳሶች በአግባቡ ለአጥቂዎች ማድረስ አለመቻላቸውን ተከትሎ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ቆይተዋል በአንፃሩ አቃቂ ቃሊቲዎች በተሻለ ከተከላካይ ጀርባ ተደጋጋሚ ሩጫዎችን በማድረግ ጎል ለማግኘት ቢሞክሩም ሀሳባቸው ብዙም ስኬታማ መሆን አልቻለም። ይሁን እንጂ በአንድ አጋጣሚ በጨዋታው መጠናቀቂያ ወቅት እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርገው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል።
እንጅባራ ከተማ ከ ጉለሌ ክ/ከ – ምድብ ለ
የምድብ \’ለ\’ የመጀመሪያ ጨዋታ እንጅባራ ከተማን ከጉለሌ ከተማ ያገናኘ ነበር። ኳስን በመቆጣጠር መነሻቸው በመስመር በኩል በማድረግ መንቀሳቀስን የጀመሩት እንጅባራዎች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ደርሰው በተደጋጋሚ መታየት ቢችሉም ከፊት ተሰልፈው የሚገኙ ተጫዋቾች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ይታይባቸው ስለነበር ያገኛቸውን ግልፅ ዕድሎች ለመጨረስ አልታደሉም። ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች እና አመዛኙን የጨዋታ ጊዜ መሀል ላይ ሲያሳልፉ የነበሩት ጉለሌዎች ከጎሉ ጋር ያደርጉት የነበረው ጥምረት እምብዛም ነበር።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ መሀል ሜዳ ላይ የሚታይባቸውን ክፍተት የደፈኑት እንጅባራ ከተማዎች ቅያሪያቸው ተሳክቶ 76ኛው ደቂቃ ላይ አብርሃም ምህረት በጥሩ ዕይታ የጉለሌን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች አቋቋምን ተመልክቶ የሰጠውን ዳዊት ታደለ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከደቂቃዎች በኋላ በአቤሴሎም አፈወርቅ ጉለሌዎች አቻ የሚሆኑበትን ዕድል አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው በ1ለ0 የእንጅባራ የበላይነት ተጠናቋል።
ሀምበሪቾ ዱራሜ ከ ሮቤ ከተማ – ምድብ
የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ በሀምበሪቾ ዱራሜ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና በግብ ሙከራም ተሽለው የተገኙበት አጋማሽ ሲሆን በሮቤ ከተማ በኩል ወደ ኋላ በማፈግፈግ መከላከልን ትኩረት በማድረግ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲጥሩ ታይተዋል። በሀምበሪቾ ዱራሜ በኩል የመሀል ሜዳ ተጫዋቹ አቤል ዘውዱ ቁልፍ ቁልፍ ኳሶች ለመስመር አጥቂዎቹ ለነ በረከት ወንድሙ እና ቶላ ንጉሴ እያሻገረ ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ በሮቤ ከተማ በኩል እነዚህን የግብ እድል በመሀል ተከላካዮቹ ሶፊያን ገለቱ እና በወንደሰን ጎሳዬ አማካኝነት ወደ ግብ እንዳይቀየር ከፍተኛ ጥረት አርገዋል። አጋማሹም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ አንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን ሮቤ ከተማዎች ከመከላከል ባሻገር የሚገኙትን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት በወንደሰን ታደሰ እና በጌታቸው አርቱሮ አማካኝነት የግብ እድል ለመፍጠር ሲጥሩ የነበረ ቢሆንም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው በሁለቱም ክለቦች በኩል ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። ይህን ተከትሎ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በውጤቱም ሀምበርቾ ዱራሜ በተደጋጋሚ ነጥብ በመጣሉ ተፎካካሪዎቹ በነጥብ እንዲቀርቡት ሆኗል።
የ05:00 ጨዋታዎች
ቡታጅራ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ – ምድብ ሀ
ምድቡን በቀዳሚነት እየመራ የሚገኘው ንግድ ባንክን ከደረጃው ግርጌ ያገናኘው ጨዋታ ብዙ ውዝግብ አስመልክቶን በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አሰላ ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው የመጀመርያው ጨዋታ የተራዘመላቸው ቡታጅራ ከተማዎች ወደ ፊት በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ንግድ ባንኮችን ለመረበሽ ቢያስቡም ወደ ጎልነት መቀየር የሚያስችል ሙከራ አላደረጉም። ያም ቢሆን እንቅስቃሴያቸው ጥሩ የሚባል ነበር። ንግድ ባንክ ምድቡን በበላይነት እየመሩ እንደመሆናቸው ጥንቃቄን መሠረት አድርገው ኳሱን በአግባቡ አደራጅተው በመጫወት በተለይ በመስመር ያደላው እንቅስቃሴያቸው በሁለት አጋጣሚ በፈጣኑ የመስመር አጥቂ አብዱልለጢፍ ሙራድ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ለጎል ለማግኘት ጫና ያደረጉት ንግድ ባንኮች ጥረታቸው ተሳክቶ 35ኛው ደቂቃ በብሩክ ብፁአምላክ አማካኝነት የመጀመርያ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተለውጠው የመጡት ቡታጅራ ከተማዎች 52ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ዮሴፍ ደንገቶ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። የአቻነት ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ቡታጅራዎች ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ቢሞክሩም ሜዳ ላይ የሆነው በተቃራኒው ነበር። ንግድ ባንኮች 72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አባይነህ ፌኖ ግብጠባቂው የተፋውን ኳስ አግኝቶ የቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በድጋሚ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ቡታጅራዎች 82ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ዳኛቸው ዳንኤል አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል። ከዚህ ጎል መስተናገድ በኋላ ብዙ ውጥረት እና ጉሽሚያዎች የበዙበት እንቅስቃሴ ስንመለከት በተለይ የንግድ ባንክ የግብጠባቂዎች አሰልጣኝ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ ምክንያት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። በዚህ ውዝግብ መሐል ወደ ፊት የሄዱት ንግድ ባንኮች በድጋሚ የቡታጅራው ግብጠባቂ የተፋውን ኳስ አቤል ማሙሽ አግኝቶ ለንገድ ባንክ የማሸነፊያውን ወሳኝ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በምድቡ መሪዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዲስ አበባ ከተማ ከ ጂንካ ከተማ – ምድብ ለ
የጅንካ ከተማ ሙሉ የጨዋታ ደቂቃው ብልጫ የታየበት የምድቡ ሁለተኛ የዕለቱ ጨዋታ አዲስ አበባ እና ጂንካን አገናኝቶ በጭማሪ ሽርፍራፊ ሰከንድ ግብ በመዲናይቱን ክለብ አሸናፊነት ተቋጭቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ አጀማመሩ ተመጣጣኝ መልክን የያዘ ቢመስልም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን ኳስን በመቆጣጠር እና ልዩነት በመፍጠር ጂንካዎች የተለዩ ነበሩ። በአጋማሹ ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ሳምሶን ጥላሁን ያዳነበት እና ኑራ ሀሰን መነሻዋን ከቅጣት ምት ካደረገች ኳስ ሙከራን ያደረጉበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው።
ሁለተኛው አጋማሽን አዲስ አበባ ከተማን ጫና ውስጥ በመክተት ጨዋታቸውን የቀጠሉት ጂንካዎች ፍፁም ብልጫን ተጋጣሚያቸው ላይ በማሳደር ከተሻጋሪ ኳሶች ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ተስተውሏል። በመልሶ ማጥቃት በኤርሚያስ ሀይሉ ካደረጉት ሁለት ሙከራዎች ውጪ ስህተቶች የተበራከተባቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ሳምሶን አሰፋን የሚፈትኑ በርካታ ሙከራዎችን አስተናግደዋል። ጨዋታው 82ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው አቤኔዘር ቾንቤ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የዕለቱ ዳኛ እያሱ ፈንቴን አላስፈላጊ ንግግር በመናገሩ በቀይ ካርድ ተወግዷል። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች የጂንካዎች የበላይነት ታይቶ የነበረ ቢሆን በጭማሪ 90+5 ተቀይሮ የገባው የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ አጥቂ ታሪኩ ጎጀሌ በመልሶ ማጥቃት የደረሰችውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ አሰልጣኝ ፓውሎስ ጌታቸው በግል ጉዳይ ያልመሩትን አዲስ አበባን 1ለ0 አሸናፊ በማድረግ ጨዋታው ተጠናቋል።
የ08:00 ጨዋታዎች
ዱራሜ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ – ምድብ
ከሰዓት ዱራሜ እና ሀላባን ያገናኘው እና ብዙም ሳቢ ያልነበረው ጨዋታ በዱራሜ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ቡድኖቹ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ የመጣር ዝንባሌዎች ቢያሳዮም በተሻላ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ሀላባ ከተማዎች ነበሩ። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ዱራሜዎች ተቀይሮ በመግባት እና በእንቅስቃሴም ልዩነት ሲፈጥር የቆየው መሐመድ ዩሐንስ በ68ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። በዚህች ጎል የተነቃቁት ዱራሜዎች በጥብቅ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት አደጋ ቢፈጥሩም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። በመጨረሻው ደቂቃ ሀላባዎች በሙሉ ኃይላቸው የአቻነት ጎል ለማግኘት ያደረጉት መታተት ስኬታማ ሳይሆን በዱራሜዎች አንድ ለምንም ለመሸነፍ ተገደዋል።
ከምባታ ሺንሺቾ ከ ካፋ ቡና – ምድብ ለ
ከምባታ ሺንሺቾን ከካፋ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን ተጠናቋል። በአሰልጣኝ መኮንን ገላነህ የሚመሩት ከምባታ ሺንሺቾዎች ኳሱን በራሳቸው እግር ስር ረጅሙን ደቂቃ በማድረግ በካፋ ላይ የበላይነትን ቢይዙም የቀድሞው የሀዋሳ ፣ ደደቢት እና ድሬዳዋ አጥቂ የነበረው በረከት ይስሀቅ ግብ አስቆጥሮ ካፋን መሪ አድርጓል። ኳስን ይቆጣጠሩ እንጂ በሙከራ ረገድ በተጋጣሚያቸው የተበለጡት ሺንሺቾዎቾ 1ለ0 እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ መቀጠል ሲችል አሁንም ልዩነት ለመፍጠር ብልጫን ወስደው በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በግብ ሙከራ ረገድ ሺንሺቾዎች በአማካይ እና አጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቻቸው ዕገዛ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረቶች ቢያደርጉም ጨዋታው በ1ለ0 የካፋ ቡና ድል አድራጊነት ፍፃሜን አግኝቷል።
አርሲ ነጌሌ ከ ኦሜድላ – ምድብ ሐ
በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ የአርሲ ነጌሌ ፍፁም የበላይነት የታየበት እና በሁሉም ነገር በልጠው የተገኙበት አጋማሽ ሲሆን ጨዋታው ከተጀመረበት ሰአት አንስቶ በቱፋ ተሽቴ አማካኝነት ነጌሌ አርሲን መሪ ለማድረግ በተደጋጋሚ የኦሜድላዎችን ግብ ሲፈትሽ የነበረ ሲሆን እንዲሁም በአማካኝ ክፍሉን ሰለሞን ገመቹ በጥሩ ሁኔታ ሲመራ ተስተውሏል። በኦሜድላ በኩል የፊት መስመር አጥቂያቸው ቻላቸው ቤዛ አንዳንድ ሙከራዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት አከባቢ ቱፋ ተሽቴ አክርሮ የመታትን ኳስ ከመእረብ በማዋሀድ ነጌሌ አርሲን መሪ ማድረግ ችለዋል። በ43ኛ ደቂቃ ላይ ያሬድ መሀመድ በግል ጥረት ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር የነጌሌ አርሲን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። አጋማሹም በነጌሌ አርሲ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ነጌሌ አርሲዎች በሰፊ ልዩነት ኳስን አግራቸው ስር በማቆየት የጨዋታውን የበላይነት በመውሰድ ጥሩ እና ለአይን ሳቢ የሆነ ጨዋታን በማሳየት ጨዋታውን ከእረፍት በፊት ባስቆጠሩት ግብ በማሸነፍ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
የ10:00 ጨዋታዎች
ሰንዳፋ በኬ ከ ጋሞ ጨንቻ – ምድብ ሀ
የዕለቱ የምድብ \’ሀ\’ የመጨረሻ ጨዋታ የሰንዳፋ በኬን ከጋሞ ጨንቻ አገናኝቶ በጋሞ ጨንቻ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።
ገና በጨዋታው ጅማሬ 6ኛው ደቂቃ ጋሞ ጨንቻዎች በአማካይ ደሳለኝ አሎ ከሳጥን ውጭ በተመታች ኳስ ጎል ማግኘት ችለዋል። ቀድሞ ጎል ይቆጠርባቸው እንጂ በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት በመሄድ ጎል ለማግኘት የሞከሩት ሰንዳፋ በኬዎች ጠንካራውን የጋሞ ጨንቻ ተከላካዮችን በማለፍ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል።
ጋሞ ጨንቻዎች በመሐል ሜዳ ላይ ብልጫ በመውሰድ ወደ መስመር በሚጣሉ ኳሶች መሪነታቸውን ለማስፋት በተለይ በመስመር አጥቂው ተስፋዬ ፍለቴ አማካኝነት አደጋ ሲፈጥሩ ቢስተዋሉም በረባውም ባረባውም ሰዓት ለማባከን በተደጋጋሚ ይወድቁ የነበሩ በመሆኑ የጨዋታውን እንቅስቃሴ አደብዝዞታል። የማጥቃት ሽግግራቸው በሚፈልገ ልክ ያልነበረው ሰንዳፋ በኬዎች በቀጥተኛ ኳሶች ወደግብ ለመድረስ ሞክረዋል። ሆኖም ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው በጋሞ ጨንቻ አንድ ለምንም ተሸንፈው ወጥተዋል።
ቂርቆስ ክ/ከ ከ ሻሸመኔ ከተማ – ምድብ ለ
አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በቅጣት በማጣታቸው በረዳት አሰልጣኞቹ እየተመራ ጨዋታውን ያደረገው ሻሸመኔ ከተማ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት ሦስት ነጥብ በመሸመት ጨዋታውን አገባዷል። የእንቅስቃሴ ብልጫውን ቂርቆስ ክፍለ ከተማዎች መያዝ ቢችሉም የሚቋረጡ ኳሶቻቸው መበራከታቸው ግብ እንዲቆጠርባቸው ሆኗል። 15ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የጨዋታ መንገድ የተገኘን ዕድል አማካዩ ጌትነት ተስፋዬ የራሱ ጥረት ታክሎበት ግብ አስቆጥሮ ሻሸመኔን ቀዳሚ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫን ማሳየት ቢችሉም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመግባት ይቸገሩ የነበሩት ቂርቆሶች 54ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ በእጆ ኳስን በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጌትነት ታፈሰ ወደ ጎልነት ለውጧት የሻሸመኔን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል። በጅብሪል ናስር ከሚመራው የመሀል ክፍል መነሻቸውን በማድረግ የመጨረሻውን ሀያ ደቂቃ ጫና ለመፍጠር ቂርቆሶች ጥረት ውስጥ ቢገቡም የሻሸመኔን ተከላካይ ለማለፍ በመቸገራቸው ጨዋታው 2ለ0 ተደምድሟል። ሻሸመኔ ነጥቡን ወደ 28 ከፍ በማድረግ ከመሪው አዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥቡን በማስተካከል በሁለተኝነት ተቀምጧል።
የካ ክ/ከተማ ከ ዳሞት ከተማ – ምድብ ሐ
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እልህ የበዛበት እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ሲሆን ከጨዋታው መጀመር አንስቶ የካ ክ/ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ እና በግብ ሙከራም ተሽለው የተገኙ ነበሩ። ይህንን ተከትሎ በ23ኛው ደቂቃ ኃይልሽ ፀጋዬ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ሆኖም ግን ከሁለት ደቂቃ በኋላ ዳሞት ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን የግብ እድል በደረጀ ነጋሽ አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር አቻ መሆን ችለዋል። የመጀመሪያ አጋማሽም በአቻ ውጤት በመጠናቀቅ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ አንደ መጀመሪያው አጋማሽ የየካ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት ቢሆንም በ48ተኛው ደቂቃ ላይ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን የመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመቀየር ሲጥሩ የየካ ክ/ከተማዎች ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶባቸው የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሱልጣን አብዬ ወደ ግብ በመቀየር ዳሞት ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የካ ክ/ከተማዎች ይበልጡኑ ተጭነው በመጫወት በ64ተኛ ደቂቃ ላይ ብስራት በቀለ በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር የካ ክ/ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል።