የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ18ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጠናቀቅ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-0 መርታት ችሏል።

አዳማ ከተማ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የተሳካ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር። በአዳማዎች በኩል 11ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ ከቀኝ መስመር ያሻማችው እና ጽዮን ፈየራ በግንባሯ ሳታገኘው የቀረችው ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ገብርኤላ አበበ እና ዓይናለም ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ ያደረጉት ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ በአጋማሹ የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል አዳማዎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሳባ ኃ/ሚካኤል ከግራ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ሳሮን ጎሳ አስቆጥራዋለች። በጨዋታው መሃል የቅዱስ ጊዮርጊሷ ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዳ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል ስታመራ ሌላኛዋ የቡድን አጋሯ ቤተልሔም ስለሺ 98ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥራ ለእንስት ፈረሰኞች አንድ ነጥብ አስገኝታለች። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ 1-1 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ

በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር አርባምንጭ ከተማ እና ንፍስ ስልክ ላፍቶ ሲገናኙ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የታጀበ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ንፋስ ስልኮች 5ኛው ደቂቃ ላይ በሬዱ በቀለ ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት ችለው ነበር። ሆኖም ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው ብልጫ እየወሰዱ የመጡት አርባምንጮች 18ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ቤተልሔም ታምሩ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ለይላ ሸሪፍ መልሳባታለች።

37ኛው ደቂቃ ላይም መሠረት ወርቅነህ ግብ አስቆጥራ አዞዎቹን አቻ ስታደርግ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ቤተልሔም ግዛቸው ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ቤተልሔም ታምሩ በግንባሯ በመግጨት ኳሱን ከግብ ጠባቂዋ ማሳለፍ ብትችልም ኢየሩሳሌም ታደሰ በግሩም ፍጥነት በግንባሯ በመግጨት አስወጥታዋለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት 1-1 ተጠናቋል።

\"\"

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በብዙዎች ዘንድ በጉጉት በተጠበቀው እና በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል በተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። 14ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀምበት የቀረችው ኳስ የመጀመሪያው የጠራ የግብ ዕድል ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ባስቆጠረችው ግብ ንግድ ባንኮች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ ሙከራቸውን 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ሰላማዊት ጎሣዬ ከረጅም ርቀት በግሩም ሁኔታ አክርራ በመምታት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል።

36ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ያቀበለቻትን ኳስ የተቆጣጠረችው አረጋሽ ካልሳ በግሩም አጨራረስ አስቆጥራው የንግድ ባንክን መሪነት ስታጠናክር እና ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በርካታ የግብ ዕድሎች መፍጠራቸውን ሲቀጥሉ 43ኛው ደቂቃ ላይም ሎዛ አበራ በቄንጥ ያቀበለቻትን ኳስ እየገፋች በመውሰድ በሳጥኑ የግራ ክፍል የገባችው አረጋሽ ካልሳ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳትጠቀምበት ስትቀር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ኤሌክትሪኮች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ዓይናለም አሳምነው ከቀኝ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ትንቢት ሳሙኤል ኳሱ አየር ላይ እንዳለ በመምታት ያደረችው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባት የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ 65ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኳ ምንትዋብ ዮሐንስ እና የንግድ ባንኳ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና በመጋጨታቸው ታሪኳ በርገና አስደንጋጭ ጉዳት ስታስተናግድ ለስድስት ያህል ደቂቃዎች ጨዋታው እንዲቋረጥ ባስገደደው ድርጊት ድጋፍ ለመስጠት ወደሜዳ የገቡት የሌላ ክለብ ወጌሻዎች እና ተመልካች የነበሩ የህክምና ባለሙያዎች የሚበረታታ ርብርብ አድርገዋል። 85ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ድንቅ የቅጣት ምት አስቆጥራ የባንክን መሪነት ወደ ሦስት ግብ ልዩነት ከፍ ስታደርግ በመጠኑ እየተሻሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮችም የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ በትንቢት ሳሙኤል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።