ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ ጉዞውን አጠናክሯል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ አራት ጨዋታዎች ሲደረጉ መሪው ሻሸመኔ ከተማ አንደኝነቱን ያጠናከረበትን ውጤት ሲያሳካ አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ጥሏል።

\"\"

አዲስ አበባ ከተማ ከመሪው ጋር ያለውን ነጥብ ማጥበብ የሚችልበትን ዕድል መጠቀም ሳይችል የቀረበትን ውጤት አስመዝግቧል። ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ እንቅስቃሴን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ከሙከራዎችም አንፃር የተገደበ ስሜት የነበረው ነበር ማለት ይቻላል 10ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ጠባቂ ስህተት ያገኛትን ጎል አጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ ወደ ጎልነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ አድርጓል። ተጋጣሚው እንጅባራ ከተማ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ እንቅስቃሴ አጥቂው የሺዋለስ በለው በመጠቀም ለማስቆጠር ቢጥሩም ከጎል ጋር መገናኘት ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት ጨዋታ ሲቀጥል በብዙ መልኩ ጎሎችን ለማስቆጠር በማራኪ እንቅስቃሴ የታጀበ የሜዳ ላይ ቆይታን በማሳለፍ እንጂባራዎች ተሽለው የቀረቡብን ሒደት ተመልክተንበታል። ኤርሚያስ ሐይሉ ካደረጋት ሙከራ በኋላ ወደ እንጂባራ የግብ ክልል ለመግባት የተቸገሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስተናግደዋል። ተቀይሮ የገባው ዳዊት ታደለ ከግራ የመዲናይቱ የግብ አቅጣጫ ወደ ውስጥ የግል አቅሙን በሚገባ ተጠቅሞ የላካትን ኳስ ወጣቱ አጥቂ የሺዋስ በለው የልጅነት ክለቡ መረብ ላይ አሳርፏታል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ እንጂባራዎች በዳዊት ታደለ ግብ ተደጋጋሚ ያገኙ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በመባሏ በመጨረሻም ጨዋታው 1ለ1 ተቋጭቷል።

የዕለቱ ሁለተኛ በነበረው የቂርቆስ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ አጀማመሩ ወደ ይርጋጨፌዎች ያደላ ብልጫን አሳይቶን የነበረ ቢመስልም የተለመደውን የኳስ ቁጥጥራቸው በሒደት እየያዙ የመጡት ቂርቆሶች በተጋጣሚያቸው ላይ ጫናን ማሳደር ጀምረዋል። ቂርቆሶች በመጀመሪያው አጋማሽ በነበራቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መጠቀም ካልቻሉበት ሙከራ ውጪ ቀዳሚው አጋማሽ ብዙም የጎሉ ጥቃቶትን አላስመለከተንም ነበር።

\"\"

በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ጨዋታው ተመልሶ ከጨዋታ ጨዋታ እየወረዱ የመጡት ይርጋጨፌ ቡናዎች በቂርቆሶች የበላይነት ተወስዶባቸው ግብም አስተናግደው ወጥተዋል። በሦስት ፈጣን አጥቂዎች በመታገዝ በማጥቃቱ ከፍተኛ ተሳትፎን ሲያደርጉ የነበሩት የአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ ተጫዋቾች 76ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የመቐለ አማካይ አሸናፊ ሀፍቱ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ አብዱልመጅድ ሁሴን ቡድኑ ቀዳሚ አድርጓል። ተጨማሪ ጎል ለማከል አሁንም ቂርቆሶች አጠናክረው ቀጥለው አብዱልመጅድ ሁሴን በጥሩ ዕይታ ያሳለፈለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ ክብሮም ፅዱቁ ወደ ጎል ለውጧት ጨዋታው በቂርቆስ አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል።

ሻሸመኔ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ የሚያደርገውን ግስጋሴ የሚያጠናክር ድልን በከምባታ ሺንሺቾ ላይ አስመዝግቧል። በጨዋታው መሐል ሜዳው ላይ ከጌትነት ተስፋዬ እግር በሚነሱ የመሬት ለመሬት ኳሶች ሁለት ፈጣን የመስመር አጥቂ በሆኑት አብዱልከሪም እና ፉዓድ ለመጠቀም አልመው የተንቀሳቀሱት ሻሸመኔዎች 23ኛው ደቂቃ ደቂቃ ከቀኝ ወደ ግራ ፉዓድ ያሻገረለትን አብዱልከሪን ቃሲም ወደ ጎልነት በመቀየር ሻሸመኔን 1ለ0 አድርጓል። አልፎ አልፎ ከርቀት በሚያደርጓቸው ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜን ለመፈተን ሺንሺቾዎች ሙከራ ቢያደርጉም ከነበረባቸው ደካማ የአጨራረስ ብቃት አንፃር ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 34ኛወሰ ደቂቃ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ጌትነት ተስፋዬ ያሾለከለትን ፉዓድ መሐመድ ግብ ጠባቂን ሁሉ አቅጣጫ በማስቀየር ከመረብ አዋህዷታል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ቴዲ ታደሰን ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ በተወሰነ ረገድ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሺንሺቾዎች በሚጥሩበት ሰዓት ተጨማሪ ጎል ሊያስተናግዱ ተገደዋል። 79ኛው ደቂቃ ሳምሶን ተሾመ ከአሸናፊ ጥሩነህ የደረሰውን ኳስ ከርቀት አስቆጥሮ ነው ማስቆጠር የቻለው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ መደበኛው መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ የሻሸመኔው ግብ ጠባቂ ታምራት ዳኜ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ሺንሺቾን ከመሸነፍ ያላዳነች ብቸኛ የማስተዛዘኛ ጎልን ድልነሳው ሽታው አስቆጥሮ በ3ለ1 የሻሸመኔ አሸናፊነት ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። ድሉም ሻሸመኔን ከተከታዩ አዲስ አበባ ከተማ በአስር ነጥብ ልዩነት መሪነቱን እንዳይጠናከር አድርጎታል።

\"\"

የቀኑ የማሳረጊያ በነበረው የጂንካ ከተማ እና አምቦ ከተማ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረች ጎል ጂንካ ከተማን ከሦስት ነጥብ አራርቃ ሁለቱን ያሳጣችበትን ውጤት ተመልክተናል። ጨዋታ ቀዝቃዛ ይዘት የነበረው ቢሆንም በተወሰኑ እንቅስቃሴዎቻቸው ጂንካዎች የተሻሉ መሆን ቢችሉም በመልሶ ማጥቃት ነቢል አብዱልሰላም 14ኛው ደቂቃ ላይ አምቦን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውን ቀስ በቀስ እየተቆጣጠሩ ጫናን በተጋጣሚያቸው ላይ ማሳየትን የጀመሩት ጂንካዎች በመልካሙ ፉንዱሬ ግብ አቻ ሆነዋል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ተሻምታ ማኑሄ ጌታቸው ያመቻቻትን ኳስ ተጠቅሞ መልካሙ ፉንዱሬ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። ብዙም ሳቢነት ያልታየበት ጨዋታውም 87ኛ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ግዛቸው ሐይሉ አምቦን አንድ ነጥብ ማስገኘት የቻለች ማራኪ ጎልን አስቆጥሮ ጨዋታው 2ለ2 መቋጨት ችሏል።

\"\"