መረጃዎች | 76ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድተዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር 28 እና 21 ነጥቦችን በመያዝ 4ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ሀዋሳ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማን ሲያገናኝ ኃይቆቹ ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ሠራተኞቹ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከመጨረሻዎቹ 11 ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ በመርታት ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ11 ነጥቦችን ርቀው የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን በመቀመጫ ከተማው እየተወዳደረ የሚገኘውን አዳማ ከተማን 2-0 ሲረቱ ያሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ በነገው ዕለትም ይጠበቃል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደው ቡድኑ በስድስተኛው እና በሰባተኛው ሳምንት ብቻ ተከታታይ ድል ያስመዘገበ ሲሆን በነገው ዕለትም እንደነዚህ ሳምንታት ተከታታይ ድል ለመቀዳጀት ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።
\"\"
በሊጉ ካደረጉት ስኬታማ አጀማመር ቀስ በቀስ እየተንሸራተቱ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ከሜዳ ውጪ ባሉ ጉዳዮች በታመሰው የቡድናቸው የጨዋታ ስሜት ጥሩ አለመሆን ምክንያት ካለፉት 10 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 30 ነጥብ  አንዱን ብቻ በመርታት አምስቱን አቻ ሲወጡ በአራቱ ተሸንፈው ያሳኩት 8 ነጥብ ብቻ መሆኑ ከነበሩበት ከወገብ በላይ ደረጃ ተንሸራተው ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ብቻ ርቀው እንዲገኙ አስገድዷቸዋል። ቡድኑ ካንዣበበበት የወራጅ ቀጠና ለመሸሽም በነገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማዎች ወንድማገኝ ኃይሉ እና ብርሀኑ አሻሞን በጉዳት አብዱልባሲጥ ከማልን ደግሞ በቅጣት በነገው ጨዋታ ሲያጡ ወልቂጤዎች በበኩላቸው ውሀብ አዳምስ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እንዲሁም ቴዎድሮስ ሀሙን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ አድርገዋል። ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸውን ያልመሩት አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እሁድ ስብስቡን የተቀላቀሉ ሲሆን በነገው ጨዋታም እንደተለመደው ቡድኑን የሚመሩ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአምስት ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ሁለቱን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ አንዱን ሲያሸንፉ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

አባይነህ ሙላት በመሀል ዳኝነት ዳዊት ገብሬ እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት እንዲሁም ሙሉቀን ያረጋል አራተኛ ዳኛ ሆነው ይህን ጨዋታ ይመራሉ።

ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

በምሽቱ መርሐግብር በ አምስት ነጥቦች እና በዘጠኝ ደረጃዎች ተበላልጠው 14ኛ እኛ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ሲገናኙ ሲዳማዎች ካሉበት የወራጅ ቀጠና ለመውጣት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ናፍቋቸው ያገኙትን ድል ለማስቀጠል የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ባለፈው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ከድል ጋር ለመታረቅ ተቃርበው የነበሩት ሲዳማዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ባስተናገዱት ግብ ሙሉ ነጥብ ሳያሳኩ ቀርተዋል። ከለገጣፎ ለገዳዲ (46) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ ግብ (30) ያስተናገደው ቡድኑ በተቃራኒው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ በሁለቱም ፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባው ይጠቁማል። በነገው ጨዋታም ከድል ከተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል ባለመሆኑ ይዘውት የሚገቡት የጨዋታ መንገድ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተከታታይ አምስት የአቻ ውጤቶች በኋላ ባለፈው ሳምንት ከድል ጋር ሲታረቁ ውድድሩ ሲጀመር ከተጠበቁበት ውጤታማነት አንጻር ካለፉት 10 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ መርታታቸው አሁንም የቡድኑን እንቅስቃሴ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። ሆኖም ወልቂጤ ላይ ያሳኩት ድል ለነገው ጨዋታ ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው እና ከማሸነፍ ስሜቱ በድጋሚ ላለለመራቅም የነገው ጨዋታ ላይ ብርቱ ፍልሚያ ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
\"\"
ሲዳማ ቡና ሙሉዓለም መስፍን ከጉዳት ሲመለስለት የይገዙ ቦጋለ የጉዳት ሁኔታ ግን ነገ ማለዳውን እንደሚታወቅ ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ምንም ጉዳት የሌለበት ሲሆን አማካዩ አማኑኤል ዮሐንስ ከቅጣት ይመለስለታል።

ሁለቱ ቡናዎች ከዚህ ቀደም በሃያ አምስት አጋጣሚዎች ተገናኝተው እኩል ስምንት ስምንት ጊዜ ድል ሲቀዳጁ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል።

ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ካሳሁን ፍፁም በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።