ዛሬ በሁለት ስታዲየሞች በተደረጉ ስድስት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ይርጋጨፌ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
የ04፡00 ጨዋታዎች
በአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበታል። ምንትዋብ ዮሐንስ እየገፋች በወሰደችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ስትመልስባት ያንኑ ኳሱ ያገኘችው ትንቢት ሳሙኤል አስቆጥራዋለች። 19ኛው ደቂቃ ላይ ሕይወት ዳንጊሶ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጋ በግብጠባቂዋ ተጨርፎ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲወጣባት ያ ኳስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ተሻምቶም ሕይወት በድጋሚ በግንባሯ በመግጨት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችላ ነበር። ከዚህ ደቂቃ በኋላም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ድሬዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ካገኙት የቅጣት ምት በተነሳ ኳስ በሥራ ይርዳው አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ በአጋማሹ የፈጠሩት የተሻለ የግብ ዕድል ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢመስሉም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያልተቸገሩት ኤሌክትሪኮች 34ኛው ደቂቃ ላይ ምንትዋብ ዮሐንስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ባመከነችው እና የአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ወደ ግብ ሞክራው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ በተመለሰባት ኳስ ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩባቸው አጋጣሚዎች ለመፍጠር ችለው ነበር።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ፍጹም የበላይነቱን የወሰዱት ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ አራት ግቦች አስቆጥረዋል። አጥቂዋ ምንትዋብ ዮሐንስ 51ኛው 72ኛው እና 79ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥራ ሐትሪክ ስትሠራ ተጨማሪዋን ግብ ደግሞ ሰላማዊት ጎሣዬ ከ ሰብለወንጌል ወዳጆ በተቀበለችው ኳስ ማስቆጠር ችላለች። 86ኛው ደቂቃ ላይም መሃል ሜዳው ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ሰብለወንጌል ወዳጆ ከሳጥን ውጪ አክርራ በመምታት ግሩም ሙከራ ብታደርግም የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ይርጋጨፌ ቡና በፍሬሕይወት ተስፋዬ ብቸኛ የ 72ኛ ደቂቃ ግብ ቦሌ ክ/ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።
የ08፡00 ጨዋታዎች
በአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም የአዲስ አበባ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ፈጣን እና ማራኪ እንቅስቃሴዎችን ሲያስመለክተን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመግባት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻሉ ነበሩ። ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት 20 ሴኮንድ ሳይሞላ የጊዮርጊሷ ዐይናለም ዓለማየሁ ባልታሰበ እንቅስቃሴ በቀኙ የሜዳ ክፍል በፍጥነት በወሰደችው ኳስ ያደረገችው ሙከራ በአምበሏ ሩታ ያደታ ተጨርፎ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል። ሆኖም በአንድ ደቂቃ ልዩነት አዲስአበባዎች ፈጣን ምላሽ ሲሰጡ ሩታ ያደታ ከሳጥኑ የቀኝ ከፍል ላይ ላይ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን መልሳባታለች። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ አልፎ አልፎ ፈታኝ በሆነ የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን የሚፈጥሩት አዲስአበባ ከተማዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የካቲት መንግሥቱ ባቀበለቻት ኳስ ከግብጠባቂ ጋር የተገናኘችው ቤተልሔም መንተሎ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን መልሳባት የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት እንስት ፈረሰኞቹ 45ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ቤተልሔም መንተሎ በጥሩ ክህሎት ተከላካይ አታልላ በማለፍ ያደረገችውን ሙከራ በወቅታዊ ድንቅ ብቃት ላይ የምትገኘው ግብጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን መልሳባታለች።
ከዕረፍት መልስ ጊዮርጊሶች የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 68ኛው ደቂቃ ላይ ኢየሩስ ወንድሙ እና ዐይናለም ዓለማየሁ ተቀባብለው የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ኢየሩስ ወንድሙ አስቆጥራዋለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ አምበሏ ሶፋኒት ተፈራ ከሳጥን አጠገብ ድንቅ ግብ አስቆጥራ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት አጠናክራለች። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት አዲስአበባዎች በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ሙከራ 84ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መሠረት ማሞ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶባታል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የልደታ ክ/ከተማ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
የ10፡00 ጨዋታዎች
በአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም በዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ሲገናኙ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት አዳማዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ሳጥን ውስጥ በተሠራ ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሔለን እሸቱ ስትመታ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ብታስቆጥረውም ኳሱ በሌላ ተጫዋች ሳይነካ ራሷ በድጋሚ ነክታዋለች በሚል ግቡ ሳይፀድቅላት ቀርቷል። በዚሁ አጋጣሚም አዳማ ከተማዎች በጨዋታው መሃል ክስ አስመዝግበዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ቱሪስት ለማ ከሳጥን ውጪ መታው የግብጠባቂዋን እጅ ጥሶ በገባው ኳስ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አዳማዎች ከክፍት ጨዋታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መቸገራቸውን ሲቀጥሉ 40ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ሌላ የተሻለ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ሳባ ኃ/ሚካኤል በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጠል የግብ ዕድሎችም ያልተፈጠሩበት ነበር። ሆኖም 70ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ቱሪስት ለማ ከረጅም ርቀት እየገፋች በመውሰድ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ስትመልስባት ኳሱን በድጋሚ አግኝታው መረቡ ላይ በማሳረፍ ለራሷ እና ለክለቧ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች። 83ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግሥት ዘውዴ ከሳጥኑ የቀኝ ከፍል ላይ ወደ ግብ ሞክራው በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣው ኳስ በአዳማ ከተማዎች በኩል የተሻለው ሙከራ ነበር። 90ኛው ደቂቃ ላይ ሲሣይ ገ/ዋህድ ከግብ ጠባቂ ጋር ብትገናኝም መጀመሪያ ኳሱን ለሰጠቻት ቱሪስት ለማ ማቀበሉን ቅድሚያ በመስጠት ለቱሪስት ለማ ስታቀብል ቱሪስትም በቀላሉ ብታስቆጥረውም ከጨዋታ ውጪ በሚል ግቡ ሲሻር 94ኛው ደቂቃ ላይም ራሷ ቱሪስት ለማ ሐትሪክ ለመሥራት ተቃርባ በግብጠባቂዋ ተመልሶባታል። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የተደረገው የአርባምንጭ ከተማ እና የመቻል ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ብቸኛዋን ግብም ቤተልሔም ታምሩ 51ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችላለች።