በሁለተኛው አጋማሽ መልኩን ቀይሮ የገባው ወላይታ ድቻ በስንታየሁ መንግሥቱ ብቸኛ ግብ መቻልን 1-0 በመርታት ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።
መቻሎች ኢትዮጵያ መድንን ከረታው ስብስብ ምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በማሳረፍ ዛሬ በረከት ደስታ እና እስራኤል እሸቱን ሲያስጀምሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕናው ሽንፈት የተሰለፈው ዮናታን ኤልያስን በዘላለም አባቴ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ወላይታ ድቻዎች ፈጠን ባለ ጥቃት በጀመሩት ጨዋታ መቻሎች አንፃራዊ የበላይነት አሳይተዋል። 9ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በኃይሉ ኃይለማሪያም ከመሀል ሜዳ የላከለትን ኳስ ይዞ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ቢኒያም ሲያወጣበት ቀዳሚ ሙከራ ያደረጉት መቻሎች ወደ ግራ መስመር ያዘነበሉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል።
ከጨዋታ ቁጥጥር ይልቅ በሽግግሮች ላይ ተመስርቶ በቀጠለው ፉክክር ወላይታ ድቻዎች የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቀላል አልሆነላቸውም።
መቻሎች በሌላ የግራ መስመር ጥቃት 26ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ ከበረከት ደስታ የተቀበለውን ከግራ ሳጥን መግቢያ ላይ ሞክሮ ወደ ውጪ በወጣበት እንዲሁም ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ተስፋዬ አለባቸው ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ተጨራርፎ ከጎል አፋፍ ላይ ቶማስ ስምረቱ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ሲነሳ ቀዳሚ ለመሆን ተቃርበው ነበር።
በቆሙ ኳሶች እና በእንቅስቃሴ የበላይ የሆኑት መቻሎች ተጋጣሚያቸው የተሳካ ጥቃት እንዳይሰነዝር በማድረጉም የበላይ ሆነው ባሳለፉት አጋማሽ ማብቂያ ላይ በምንተስኖት አዳነ ሌላ የግንባር ሙከራም ማድረግ ችለዋል።
ከዕረፍት መልስ ድቻዎች ተነቃቅተው ገብተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባቴ በቀኝ ዳዊት ማሞን አልፎ ባደረገው ጠንካራ ሙከራ ውብሸት ጭላሎን የፈተነ ቀዳሚ ሙከራ ማድረግም ችለዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን ግሩም ሀጎስ እና ከነዓን ማርክነህ በገጠማቸው ከባድ ግጭት ምክንያት በህክምና ዕርዳታ ረዘም ያለ ጊዜ ያለፈ ሲሆን ግሩም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል ሲያመራ ከነዓንም ጥቂት ቆይቶ ተቀይሮ ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ስንታየሁ መንግሥቱን ያማከለ ጥቃት በድቻዎች እየታየ በቀጠለው ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ክስተት ተፈጥሯል። ስንታየሁ ከተከላካዮች ጀርባ ከኳስ ጋር አምልጦ ሲገባ በቶማስ ስምረቱ ጥፋት ተሰርቶበት ወላይታ ድቻ ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኝም ቃልኪዳን ዘላለም መትቶ አምክኖታል።
በመቻሎች የመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ ቢፈተኑም ወደ ቀኝ ያደላው የወላይታ ድቻ ጥቃት በዘላለም እና ስንታየሁ ቅንጀት ታጅቦ የፈጠረው ጫና 75ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ዘላለም ከዚሁ አቅጣጫ ያደረሰውን ኳስ ስንታየሁ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ በመምታት የጦና ንቦቹን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።
ከዚህ በኋላ እስከ 102ኛ ደቂቃ ጉሽሚያዎች ሳይለዩት በቀጠለው ጨዋታው ተጠቃሽ ሙከራ ባይደረግም የመቻሎች ጥቃት እየተዳከመ ሲሄድ ጥንቃቄ እና መልሶ ማጥቃትን የመረጡት ወላይታ ድቻዎች የግብ ክልላቸውን ሳያስደፍሩ በ1-0 ድል ጨዋታውን ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረስ ይችሉ እንደነበር እና በቀጣዩ ግማሽ የገጠማቸው ጉዳቶች እንዲሁም አስገዳጅ ቅያሪዎች ተፅዕኖ መፍጠረቸውን አንስተው ተጋጣሚያቸው የኃይል አጨዋወት መምረጡንም ጠቁመዋል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው ያገኙት ሦስት ነጥብ አዳማ ላይ በትዕግስት ለደገፏቸው ደጋፊዎች መታሰቢያ እንዲሆን የሰጡ ሲሆን ቡድናቸው ያሳየው ትዕግስት ለውጤት እንዳበቃው አብራርተው የፍፁም ቅጣት ምት ለመምታት ቃልኪዳን እና ስንታየሁ መከራከራቸው ከውጤት ጉጉት እንደሆነ እና እንደምርቃት እንደሚያዩት ተናግረዋል።