ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ኢትዮጵያ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ
በዕኩል 27 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበላልጠው 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ያሉትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ቡናዎች ካሉበት የውጤት ማጣት ለማገገም ድሬዎች ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ አርባምንጭ ከተማ (10) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የአቻ ውጤት (9) ከወላይታ ድቻ ዕኩል ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከአምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወልቂጤ ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል ቢመለሱም ቀጣይ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ግን አቻ አጠናቀዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸው ጥንካሬያቸው ቢሆንም በተለይ ብዙ የተጠበቀበት የአጥቂ መስመሩ ግን በእነዚህ ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ እጅግ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው። በነገው ዕለትም ወደ ስድስተኛ ደረጃ ከፍ የሚሉበትን ድል ለማሳካት ከነርሱ በዕኩል ነጥብ ከተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ጋር ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ጠንካራ ፍልሚያ አድርገው ሀዋሳ ከተማን 1-0 የረቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳያስተናግዱ በወጡበት ጨዋታ ያሳዩት መልካም እንቅስቃሴ ቡድኑ ከገባበት የውጤት ቀውስ ውስጥ ለማገገም ጥሩ ተስፋን እንዲሰንቁ ያስችላቸዋል። አዲስ አሰልጣኝ ከሾሙ በኋላ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል የቀናቸው ብርቱካናማዎቹ ያገኙትን የአሸናፊነት መንፈስ በማስቀጠል በስምንተኛው እና በዘጠነኛው ሳምንት ብቻ ያሳኩትን ተከታታይ ድል በነገው ዕለትም ለማሳካት ከኢትዮጵያ ቡና የሚጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።
ከአስራት ቱንጆ በተጨማሪ ጫላ ተሺታ እና አብዱልሀፊስ ቶፊቅን በጉዳት ያጣው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ሮቤል ተክለሚካኤል ከጉዳት ተመልሶለታል። ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አሳንቴ ጎድፍሬድ ፣ ቢኒያም ጌታቸው እና ያሬድ ታደሠን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኝም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን 21 ጊዜ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 12 ድሬዳዋ ከተማ 4 ድሎችን አስመዝግበው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና 35 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 19 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ጨዋታውን ተካልኝ ለማ በዋና ዳኝነት ፣ ሶርሳ ዱጉማ እና ታምሩ አደም በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ምሽት 12 ሰዓት ላይ እንደሚደረግ በሚጠበቀው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ላለመራቅ ሦስት ነጥቡን እጅግ የሚፈልጉትን ባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ ተጠባቂ መርሐግብር ነው።
በውድድር ዓመቱ አምስት ተከታታይ ድሎችን ማሳካት የቻለው ባህር ዳር ከተማ ብቻ ነው። አይበገሬ ሆነው የቀረቡት የጣና ሞገዶቹ ባለፉት 5 ጨዋታዎች ላይ 15 ግቦችን የተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አሳርፈዋል። ይህም በአማካይ በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ያስቆጥራሉ ማለት ነው። በሁሉም የሜዳ ክፍል ውስጥ ከተለያዩ የተጫዋች አማራጮች ጋር በጥንካሬው የቀጠለው ቡድኑ ሊያሳስበው የሚችለው ብቸኛ ነገር ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ማስደፈሩ ብቻ ነው። ከሰሞኑ በሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ 11 ውስጥ በተከታታይነት መመረጥ የቻለው አማካዩ አለልኝ አዘነ እያሳየው ያለው ድንቅ እንቅስቃሴ በነገው ዕለትም ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ነጥቦችን ርቀው የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካታቸው ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪነታቸውን ጥያዌ ውስጥ አስገብቶታል። ቡድኑ በሚተማመንበት የአጥቂ መስመሩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ (41) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (39) ማስቆጠር ቢችልም አሁንም የሚፈጠሩ የግብ ዕድሎችን በብዛት ወደ ውጤት ከመቀየር ባለፈ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁሉ ግብ ያስተናገደውን የኋላ መስመራቸውን እንዲፈትሹ ያስገድዳል። በነገው ዕለትም በወቅታዊ ድንቅ ብቃት ላይ ከሚገኙት የጣና ሞገዶቹ ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።
ባህር ዳር ከተማ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለጨዋታው ሲደርስ ኢትዮጵያ መድንም ጉዳት ካይ ከሚገኘው አብዱልከሪም መሐመድ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም።
ሁለቱ ቡድኖች ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ግንኙታቸው ባህር ዳር ከተማ 3-2 መርታቱ ይታወሳል።
የምሽቱን ጨዋታ ለመምራት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሐል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳትነት እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።