የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ንብ ፣ እንጅባራ እና ቦዲቲ ድል ሲቀናቸው ሻሸመኔ ከተማ ነገ ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል።
ጠዋት ላይ ቀዳሚ ሆኖ የተደረገው ጨዋታ 1ለ1 ተጠናቋል። የይርጋጨፌ ቡና የእንቅስቃሴ እና የሙከራ ብልጫ በታየበት ጨዋታ ቀዳሚ መሆን የቻሉትን ግን ቀድመው መውረዳቸውን ያረጋገጡት ከምባታ ሺንሺቾዎች ናቸው። 33ኛው ደቂቃ ላይ የይርጋጨፌ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ኳስን በሳጥን ውስጥ በእጅ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ድልነሳው ሽታው ከመረብ አሳርፏታል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በይበልጥ የአጥቂ ክፍላቸውን ቁጥር በማብዛት ወደ አቻነት ለመምጣት ጥረት ያደረጉት ይርጋጨፌ ቡናዎች 67ኛ ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ኪሮስ ከቅጣት ምት ባስቆጠራት ማራኪ ጎል 1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገደዋል።
ቀጥሎ 5 ሰዓት ሲል ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያሳየን የንብ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ለዕይታ ማራኪ በሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ታጅቦ ንብን ከሦስት ነጥብ ጋር አገናኝቶ ተጠናቋል። በጥሩ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ንቦች 19ኛው ደቂቃ ገደማ እዮብ ደረሰ ያስቆጠራት ቆንጆ ጎል ቡድኑን መሪ እንዲሆን አስችላለች። በቶሎ በሽግግር ምላሽ ለመስጠት የዳዱት ቂርቆሶች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በአብዱልመጅድ ሁሴን ግብ አቻ ሆነዋል። ፈጠን ያሉ እንቅሰቃሴዎችን ያስተናገደው ጨዋታው አሁንም ከሦስት ደቂቃ መልስ ጎል ተቆጥሮበታል። በሳጥን ውስጥ ኳስ መነካቷን ተከትሎ ኤልያስ እንድሪያስ ወደ ጎልነት ለውጧት በድጋሚ ንብን መሪ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ በአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ የሚመሩት ቂርቆሶች በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ወደ ጨዋታ ለመመለስ ትግል ማድረግ ቢችልም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችሉ በንብ 2ለ1 ተረተዋል።
ስድስት ግቦች የተስናገዱበት የአምቦ ከተማ እና እንጂባራ ከተማ ጨዋታ በመጨረሻም እንጂባራን አሸናፊ አድርጎ አምቦን ወደ አንደኛ ሊግ አውርዶ ተገባዷል። እንጂባራዎች ባደረጉት ፈጠን ያለ የመስመር አጨዋወታቸው ታግዘው በአብርሃም አሰፋ እና በሙከረም ሁለት የርቀት ጎል የመጀመሪያውን አጋማሽ 2ለ0 ፈፅመዋል። ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥልም በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ብልጫ መውሰዳቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ አዲሱ ዶይሶው እንጂባራዎች ተቀይረው በገቡት ዳዊት ታደለ አስደናቂ ግብ እንዲሁም በምትኩ ማመጫ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል የግብ መጠናቸውን ወደ አራት አሳድገዋል። የጨዋታው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎችን መንቃት የጀመሩት አምቦዎች በነቢል አብዱልመጅድ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ቢችሉም ጨዋታው 4ለ2 የእንጂባራ ድል አድራጊነት ተደምድሟል። በውጤቱም አምቦ ከተማ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን ለመውረድ ተገዷል።
የቦዲቲ ከተማ ታታሪነት በወጥነት በተንፀባረቀበት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን 2ለ1 አሸንፈው በመውጣታቸው ሻሸመኔ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገበትን ውጤት አሳክቷል። ጨዋታውን በራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገው የጀመሩት ቦዲቲዎች 27ኛው ደቂቃ ላይ በማሞ አየለ ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። ጨዋታው ዳግም በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስም ቦዲቲዎች ማሞ አየለ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎልን አክሏል።
መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊገባደድ አስር ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ ወደ ጨዋታ ቅኝት ራሳቸውን ያስገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች በሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሙሉቀን ታሪኩ አማካኝነት ብቸኛ ጎልን አስቆጥረው ጨዋታው 2ለ1 በቦዲቲ አሸናፊነት ተቋጭቷል። የአዲስ አበባን መረታትም ተከትሎ ሻሸመኔ ከተማ ነገ ጨዋታው ከማድረጉ አስቀድሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል።