የሱራፌል ጌታቸው እና ቢንያም ጌታቸው የመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች ብርቱካናማዎቹን ሦስት ነጥብ አስጨብጠዋል።
ብርቱካናማዎቹ ባለፈው ጨዋታ ከተጠቀሙበት ቀዳሚ ስብስብ ፍሬው ጌታሁን ፣ ያሲን ጀማል ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ዳዊት እስቲፋኖስ እና ሙህዲን ሙሳን ፤ በዳንኤል ተሾመ ፣ መሐመድ አብዱለጢፍ ፣ አቤል አሰበ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ቢንያም ጌታቸው ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በመድን ከተሸነፈው ስብስብ ጉዳት የገጠመው ፀጋ ደርቤን በኢብራሂም ከድር ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።
በመጀመርያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድምያ ሰጥተው ለመጫወት የሞከሩበት ፤ ኤሌክትሪኮች ደግሞ በአንፃሩ የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት በመመከት አልፎ አልፎ ደግሞ ኳሱን ለመቆጣጠር በመሞከር አብዛኛው የአጋማሹ ግዜ አሳልፈዋል።
በጨዋታው ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በሁለት አጋጣሚዎች በቢንያም ጌታቸው አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል ፤ በተለይም አጥቂው ከኤልያስ የተላከለትን ኳስ ገፍቶ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በመምታት ግብ ጠባቂው ያዳነው ሙከራ የአጋማሹ ወርቃማ ዕድል ነበር። ድሬዳዋዎች ከሙከራው በኋላም በዮሴፍ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ አድርገዋል።
በአጋማሹ በአመዛኙ በመከላከል ላይ የተጠመዱት ኤሌክትሪኮች ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ወደ ሙከራነት የተቀየረው ግን አንዱ ብቻ ነበር። ሙከራውም አብነት ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው እንደምንም አውጥቶታል።
ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተው ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴም በሙከራም ደረጃ በአንፃራዊነት የተሻለ ፉክክር የታየበት ነበር። በአጋማሹ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በቻርለስ ሙሴጌ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። አጥቂው ቢንያም ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ መንገድ አዙሮ በመምታት ነበር ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገው። ጋዲሳ በግሩም መንገድ ከቅጣት ምት መቶት በጨዋታው በርካታ ሙከራዎች ያዳነው ካክፖ በጥሩ መንገድ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራም ሌላ ብርቱካናማዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ሙከራ ነበር።
በአጋማሹ የመጀመርያው አጋማሽ በተለየ መንገድ ለማጥቃት የሞከሩት ኤሌክትሪኮች ከድሬዳዋ ተከላካዮች ጀርባ የነበረው ሰፊ ክፍተት ለመጠቀም ያለሙ ቅያሬዎች ቢያደርጉም በርካታ ጠሩ የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በሙሴ አማካኝነት ወርቃማ ዕድል አምክነዋል ፤ አማካዩ ዮናስ አሻምቶት አብዱለጢፍ የጨረፈው ኳስ ነፃ ሆኖ ብያገኝም ሙከራውን የግቡን አግዳሚ መልሶበታል። ኤሌክትሪኮች ወርቃማው ሙከራ በኋላም በአለን አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርገዋል ፤ አጥቂው አብነት በጥሩ መንገድ ያቀበለው ኳስ ቢመታውም ግብ ጠባቂው እንደምንም አድኖታል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ብርቱካናማዎቹ በቢንያም አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ችለዋል ፤ ሙህዲን ሙሳ ከኤሌክትሪክ ተከላካዮች እግር ስር ኳስ ነጥቆ ለቢንያም አቀብሎት አጥቂው በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሯል። ከደቂቃዎች በኋላም በግራ መስመር አከባቢ የተገኝውን ቅጣት ምት ተጠቅሞ ሱራፌል ጌታቸው በቀጥታ ግብ በማስቆጠር የድሬዳዋ ከተማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በቅድሚያ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ ስምዖን አባይ በጨዋታው ኳሱን ለመቆጣጠር ሙከራ አድርገናል ፤ በመጨረሻው ደቂቃ ትኩረታችን በማጣታችን በተከታታይ ግብ ተቆጥሮብናል ካሉ በኋላ በማጥቃት ክፍል የነበራቸው እንቅስቃሴ አመርቂ እንዳልነበር ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም \”በእግር ኳስ ተስፋ የሚስቆርጥ ነገር የለም ግን ከባድ ሁኔታ ነው ያለነው\” ብለዋል። የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ በጥንቃቄ ለመጫወት መሞከራቸው ገልፀው በጨዋታው በመከላከል ላይ ጥሩ እንደነበሩ ተናግረዋል። ተጋጣሚያቸው ኤሌክትሪክ ቀላል ተጋጣሚ እንዳልነበር የገለፁት አሰልጣኙ የዛሬው ድል \”የበለጠ እየጠነርን እንድንሄድ የሚያደርግ ድል ነው\’ ብለዋል።