በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐግብሮች መካከል የአንድ ጨዋታ ውጤት በጊዜያዊነት እንዳይፀድቅ ሲወሰን ሁለት ክለቦች ቅጣት አስተናግደዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ ግንቦት 05 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ደረጃ ከተላለፉ ከበድ ያሉ ውሳኔዎች መካከል የባህር ዳር ከተማው አለልኝ አዘነ በጨዋታ ሳምንቱ ኃይማኖታዊ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል በውስጥ ልብሱ ደርቦ ስለመልበሱ ሪፖርት የተደረገበት ሲሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት ተጫዋቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሦስት ሺህ ብር/ እንዲሁም ክለቡ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺህ ብር/ እንዲከፍሉ ተወስኗል። በሌላ በኩል የወልቂጤ ከተማው ዋሃብ አዳምስ በሳምንቱ ጨዋታ ወቅት ከዳኛ እይታ ውጭ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን በክርን ስለ መምታቱ ሪፖርት የተደረበት ተጫዋቹ በፈጸመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 4/አራት/ ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3000 /ሶስት ሺህ / እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃም ወላይታ ድቻ በ22ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ተጫዋቾች የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም መልበሻ ክፍል ሁለት በሮች ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ክለቡ የተሰበሩትን በሮች እንዲያሰሩ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
በተጨማሪም በፕሪምየር ሊጉ አ.ማ. የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ግጥሚያ ዙሪያ ምርመራ እያደረገበት በመሆኑ የኮሚቴው የቅድመ ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የጨዋታው ውጤት እንዳይጸድቅ እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እንዲታዩ የውድድርና ሥነስርዓት ኮሚቴ ወስኗል።