በምሽቱ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 3-0 በመርታት ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቧል።
ምሽት 12፡00 ላይ የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ሲደረግ ድሬዎች በ 23ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በጋዲሳ መብራቴ ምትክ ሙኸዲን ሙሳን አስገብተው ሲጀምሩ መድኖች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት በሲዳማ ቡና 1-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሦስቱ ተከላካዮች ላይ ለውጥ አድርጓል በዚህም ፀጋሰው ድማሙ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ተካልኝ ደጀኔ በ ያሬድ ካሳዬ ፣ ቻላቸው መንበሩ እና ቴዎድሮስ በቀለ ተተክተው ጀምረዋል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት ሂደት ጨዋታውን ማስኬድ የቻሉት መድኖች 6ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ብሩክ ሙሉጌታ ከግራ መስመር እየገፋ በወሰደው ኳስ አንድ ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሀቢብ ከማል መሬት ለመሬት ያደረገው ሙከራ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። 15ኛው ደቂቃ ላይም ራሱ ሀቢብ ከማል ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ አስወጥቶበታል።
ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በቁጥር በመብዛት በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረው የተቸገሩት ድሬዎች ይባስ ብሎም ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ከተከላካዮች ጀርባ አፈትልኮ የወጣው ወገኔ ገዛኸኝ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ኃይል በቀላቀለ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ዕድለኛ አድርጓቸዋል። ይህም በመድኖች በኩል የመጀመሪያው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ግብ ተቆጥሮበታል። ወገኔ ገዛኸኝ ከባሲሩ ኦማር የተሻገረለትን ኳስ መረቡ ላይ አሳርፎት በተደጋጋሚ የተደረገውን የኢትዮጵያ መድን ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው እጅግ የተፈተኑት ድሬዎች በጨዋታው የተለየ ነገር ለመፍጠር ተቸግረው ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ሲቀሩ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ መድኖች መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ወገኔ ገዛኸኝ ከብሩክ ሙሉጌታ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ መድን በአጋማሹ የነበረውን ብልጫ የሚገልፅ ትዕይንት ፈጥሯል።
ድሬዳዋ ከተማዎች በአንጻሩ በአጋማሹ አንድም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው አጋማሹ በኢትዮጵያ መድን 2-0 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ብርቱካናማዎቹ ሦስት ፈጣን ቅያሪዎችን በማድረግ በጥሩ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ በተከላካዮቹ ሲመለስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ይዞበታል። ሆኖም ይህ መነቃቃታቸው ከአስር ደቂቃዎች በላይ ሳይዘል 55ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። የመድኑ አጥቂ ሳይመን ፒተር ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ትልቁን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
66ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ኦማር በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው ፀጋሰው ድማሙ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ሲመልሰው ያንኑ ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ብሩክ ሙሉጌታ መረቡ ላይ አሳርፎት የኢትዮጵያ መድንን መሪነት ወደ ሦስት ግብ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ሦስተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸው ጥረት የከሸፈባቸው ድሬዎች በተቻኮለ እና ባልተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደፊት ለመጠጋት ቢሞክሩም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ መድኖችም በአንጻሩ ውጤቱን ለማስጠበቅ ጨዋታውን በማቀዛቀዝ ቀጥለዋል። ሆኖም 89ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋው ሄኖክ ሀሰን እንየው ካሳሁን ከቀኙ የሳጥን ጠርዝ ላይ ሆኖ ባቀበለው ኳስ ያልተጠበቀ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አሥራት አባተ ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን ገምተው እንደነበር እና በተዘጋጁት ልክ እንዳልታዩ ሲናገሩ በሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ አንዳሳዩ ግን በሚጠብቁት ልክ እንዳልነበር ሲገልጹ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ በደንብ ጠንክረው ካልሠሩ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንጻር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መድኑ ምክትል አሰልጣኝ ለይኩን ታደሰ የተጋጣሚ ቡድን ባለፈው ሳምንት ከገባበት አቀራረብ በመነሳት በመጀመሪያው አጋማሽ እንደጠበቁት ማግኘታቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ ጥሩ ነገር እንዳለ እና ስለ ቀጣዩ ጨዋታ ብቻ እንደሚያስቡ ጠቁመዋል።