ከሁለተኛው ቡድን ጋር ጥሩ ዓመት አሳልፎ የሊግ ዋንጫን ያነሳው ቤተ እስራኤላዊ አዲስ ሹመት አግኝቷል።
በእስራኤል ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ወጣቱ እና የመጀመርያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ መሳይ ደጉ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ የእስራኤሉን ታላቅ ክለብ ማካቢ ሀይፋ ለማሰልጠን ተስማምቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 15 ቀን 1986 የተወለደው ይህ ወጣት አሰልጣኝ በ1990 በኦፕሬሽን ሰለሞን አማካኝነት ቤተ-እስራኤላዊያንን ወደ እስራኤል የማጓጓዝ ሒደት አካል በመሆን ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ እሰራኤል ከሄደ በኋላ በዝቅተኛ ዲቪዝዮኖች በመጫወት አሳልፏል። መሳይ ከሀፖል ቴል ኣቪቭ አካዳሚ ወጥቶ ለአስራ ሁለት ክለቦች ከተጫወተ በኋላ በ2013 በሀያ ሰባት ዓመቱ በከባድ የቁርጭምጭሚት ጉዳት በግዜ ከስፖርቱ ተገሏል።
ወደ አሰልጣኝነት ከገባ በሁለተኛው የሊግ እርከን ሀፖይል ክፋር ሳባ ፣ ኢሮኒ ኬርያት ሻሞናና ሀፖይል ፔታህ ቲክቫ የመሳሰሉ ክለቦች ስያሰለጥን ከቆየ በኋላ በ2022 የማካቢ ሀይፋ ከ19 ዓመት በታች ቡድንን ሲረከብ ፤ ቡድኑ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ እና በቻምፒየንስ ሊግ ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፍ ረድቶታል።
ሹመቱን ተከትሎ ከክለቡ ድረ-ገፅ ጋር ቆይታ ያደረገው መሳይ \” ኮርቻለሁ ስላመናችሁኝም በጣም አመሰግናለሁ ፤ ክለቡን በቀጣይ ዋንጫዎች እንዲያነሳ መርዳት እና ክለቡን መምራት ትልቅ ስኬት ነው። ደጋፊያችንን ለማስደሰት የምችለውን አደርጋለሁ\” ብሏል።
ከቀጣይ ውድድር ዓመት ጀምሮ ታላቁን የእስራኤል ክለብ ማሰልጠን የሚጀምረው ቤት እስራኤላዊው በሻምፕዮንስ ሊግ የደመቀው ብሩክ ደጉ ታናሽ ወንድም መሆኑም ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም በቤተ እስራኤላዊው ታሪክ ዙርያ ያዘጋጀነውን ፅሁፍ ይመልከቱ : LINK [ፋና ወጊው መሳይ ደጉ በእስራኤል ታሪክ ሰርቷል]