ጠንካራ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በሀዲያ ሆሳዕና 2-1 ተረቶ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ነጥቦችን አጥቷል።
ባህርዳር ከተማ ከፈታኙ የአዳማ ጨዋታ ሦስት ነጥብን ሲያገኝ ከተጠቀመበት አሰላለፍ ፍፁም ጥላሁንን በአደም አባስ የተካበት ብቸኛ ቅያሪው ሲሆን ከወልቂጤው የአቻ ውጤት አንፃር ሀድያ ሆሳዕናዎች በአራቱ ላይ ለውጥን አድርገዋል። ብርሀኑ በቀለ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ሔኖክ አርፊጮ እና መለሰ ሚሻሞን በከረጅም ጊዜ ጉዳቱ በተነሳው ቃልአብ ውብሸት ፣ ዳግም በቀለ ፣ ሰመረ ሀፍታይ እና ብሩክ ማርቆስ ተክተዋል።
ጨዋታው ጅምሩን ያደረገው ፈጠን ባለ ሙከራ ነበር። በዚህም ሀድያ ሆሳዕናዎች ያስጀመሩት ኳስ መሐል ሜዳ ላይ በመቋረጡ የባህርዳሩ አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ አግኝቷት ከግቡ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ገና በ50ኛው ሰከንድ ወደ ጎል የመታትን ግብ ጠባቂው ፔፕ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣት ቅፅበታዊ አጋጣሚ ቀዳሚዋ የጨዋታው ሙከራ ሆናለች። ፈጣን ሙከራን ካስተናገዱ በኋላ በተረጋጋ አጨዋወት ከመሐል ክፍሉ ወደ መስመር በሚወጡ ኳሶች ሀድያዎች የጥቃት መነሻቸውን ሲያደርጉ ተስተውሏል ነገር ግን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ አጨራረሳቸው ደካማ ነበር።
16ኛው ደቂቃ ላይ ፉዓድ ፈረጃን በቻርልስ ሪቫኑ በጉዳት ለመቀየር ከተገደዱ በኋላ እንቅስቃሴያቸው የተቀዛቀዘው ባህርዳሮች ቻርለስ ሪባኑ ከርቀት ሞክሮ ፔፕ ሰይዶ ከያዘባቸው ሙከራ ውጪ የጨዋታው የሀይል ሚዛን ወደ ሀድያ ሆሳዕና ያመዘነ ሆኗል። በጣለው ዝናብ ምክንያት ለሁለቱም ቡድኖች ሜዳው አመቺ ባይሆንም መሐል ሜዳውን በፍቅረየሱስ መሪነት በመታገዝ ግብ ለማስቆጠር ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የቻሉት ሀድያዎች ከተደጋጋሚ ጥረቶች መልስ 29ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ፍቅረየሱስ መሐል ለመሐል የላከለትን ኳስ ዘካሪያስ ፍቅሬ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ወደ ውስጥ ሲያሻግር የተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው ፋሲል የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበቶበት ሠመረ ሀፍታይ ሾልኮ ወጥቶ ወደ ጎልነት ለውጧታል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባህርዳሮች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ቢሞክሩም አጋማሹ በሀድያ የ1ለ0 መሪነት ተገባዷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ተመልሶ አራት ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩ ሀድያ ሆሳዕና ሁለተኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። በፈጣን ተሻጋሪ ኳስ ዘካሪያስ በተከላካዮች መሐል የሰጠውን ወጣቱ የመስመር አጥቂ ተመስገን ብርሀኑ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት ፋሲል መረብ ላይ አሳርፏታል። ሁለት ጎልን ወደ ካዝናቸው ከከተቱ በኋላ ጥንቃቄ አዘል ጨዋታ ላይ ሀድያዎች ትኩረት ማድረጋቸው ለበባህርዳሮች ምቹነት ፈጥሮላቸዋል። በጨዋታ እንቅስቃሴ እና ከቆሙ ኳሶች ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ በብርቱ የታገሉት ባህርዳሮች ተደጋጋሚ ሙከራን አድርገዋል። ከርቀት በቻርለስ ፣ ሀብታሙ እና ዱሬሳ አከታትለው ሞክረዋል። በተለይ ዱሬሳ ሹቢሳ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ወደ ጎል መትቶ የግቡ ቋሚ ብረት ከመለሰበት ሙከራ መልስ ግብ አስቆጥረዋል።
67ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሀድያ የሜዳ ክፍል ወደ መስመር ካደላ ቦታ ላይ ቻርለስ ሪቫኑ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ የፔፕ ሰይዶ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተክሎበት ኳሷ ከመረብ ተዋህዳለች። ባህርዳሮች ወደ አቻነት ለመምጣት ፍፁም ያለቀላቸውን ዕድሎች በተጋጣሚያቸው ላይ ወስደዋል 84ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ወደ ጎል የላካትን ኳስ ግርማ በቀለ እና ግብ ፔፕ ሰይዶ ሳይናበቡ ቀርተው ዱሬሳ ሹቢሳ አግኝቷት በሚያስቆጭ መልኩ ሳይጠቀማት ቀርቷል። ባህርዳሮች እንደነበራቸው ብልጫ ተጨማሪ ጎልን ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው 2ለ1 በሀድያ አሸናፊነት ተቋጭቷል። ውጤቱም ባህርዳር ከተማ ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገደበት ሆኗል።