ሪፖርት | የሲዳማ ቡና ተከታታይ የ1-0 ድል ቀጥሏል

ሲዳማ ቡና በደስታ ደሙ ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማን 1-0 በመርታት አራተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ፋሲል ከነማ ከለገጣፎው ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርጓል። ኦሴ ማውሊ እና በዛብህ መለዮን በሽመክት ጉግሳ እና ታፈሰ ሰለሞን ሲተኩ ሲዳማ ቡና ከመቻሉ ጨዋታ አንፃር ሦስት ጉዳት ባስተናገዱ ተጫዋቾቹ ላይ ነው ለውጡን ያደረገው መክብብ ደገፉ ፣ ደግፌ ዓለሙ እና አንነተህ ተስፋዬን በፊሊፕ ኦቮኖ ፣ አማኑኤል እንዳለ እና መሀሪ መና ተክተዋቸዋል።

\"\"

ጨዋታውን ያስጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች ገና በጊዜ መሪ የሆኑበትን ግብ 2ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፈዋል። በዚህም ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል ከተገኘ ቅጣት መሀሪ መና ሲያሻማ የፋሲል ከነማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች እና ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል የሰሩትን የአቋቋም ስህተት ተከትሎ ደስታ ደሙ በቀላሉ ጎል አድርጎታል። ከጅምሩ ጎል የተቆጠረባቸው ፋሲሎች ራሳቸውን በደንብ ወደ ጨዋታ ቅኝት በማስገባት መሐል ሜዳ ላይ የሱራፌል እና ታፈሰን የንክኪ ኳሶች በተለይ ወደ ቀኝ በኩል በመለጠጥ ሽመክት ጉግሳን ባነጣጠር እንቅሰቃሴ ጎልን ለማስቆጠር በብርቱ ታግለዋል።

\"\"

መሪ መሆን ይቻሉ እንጂ በቀሩት ደቂቃዎች ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን መርጠው የተንቀሳቀሱት ሲዳማ ቡናዎች በጥብቅ መከላከል አጨዋወት ነገር ግን የፋሲልን የሚቋረጡ ኳሶች በሚያገኙበት ወቅት ፈጠን ባለ ሽግግር ለመጫወት ሞክረዋል። አፄዎቹ በድግግሞሽ በሱራፌል የርቀት ኳሶችን ሁለት ጊዜ ወደ ግብ ቢሞክሩም ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ በተመሳሳይ ሁለቱንም አጋጣሚዎች ይዞበታል። ከጎሏ ውጪ የጠሩ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት እና የፋሲል ከነማ አንፃራዊነት ጎልቶ የታየበት አጋማሽ በ1ለ0 ለዕረፍት አምርቷል።

\"\"

በሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ሲዳማ ቡና መሐል ሜዳው ላይ የነበረባቸውን ክፍተት ለማረም ሙሉቀን አዲሱን ወደ ሜዳ ሲያስገቡ ፋሲል ከነማ በበኩሉ ጎልን ለማስቆጠር ያለመ ቅያሪን ዓለምብርሀንን በኦሴ ማውሊ ተክተዋል። ፈጠን ባለ የመስመር ጨዋታ አጋማሹን የጀመሩት አፄዎቹ 46ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ወደ ጎል ከቀኝ አቅጣጫ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታ ኦሴ ማውሊ ተደርቦ ባወጣበት አጋጣሚ የሲዳማን የግብ አቅጣጫ መፈተን ጀምረዋል። በሌላ ሙከራቸው ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል አንድ ለአንድ ከግቡ ጋር ማዊሊን አገናኝቶት ጋናዊው አጥቂ በደካማ እግሩ ጥሩዋን አጋጣሚ አምክኗታል።

ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ በተጋጣሚያቸው ይበለጡ እንጂ ፈጣን መልሶ ማጥቃት ላይ አጃህን ባማከለ መልኩ ሲዳዎች ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ፋሲሎች 59ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ከናትናኤል ጋር ተቀባብሎ ናትናኤል በመጨረሻም የሰጠውን ኳስ ኦሴ ማውሊ ወደ ጎል ሲመታ ፊሊፕ ኦቮኖ በጥሩ ቅልጥፍና ከጎልነት ታድጓጋል።

\"\"

ሲዳማ ቡናዎች በተጠቀሰው የጨዋታ መንገድ አጃህን ጥሩ አጋጣሚን አግኝቶ ሳይጠቀም ቀርቶ የተመለሰችዋ ኳስን ሙሉቀን አዲሱ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ኳሷ በተከላካይ እና በቋሚው ታግዛ ወደ ውጪ ወጥታለች። ፋሲሎች 81ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ወደ ጎል ያሻማትን ኳስ ኦሴ ማውሊ በግንባር ገጭቶ የላይኛው የግቡ አግዳሚ መልሶታል። ከሰከንዶች በኋላ ናትናኤል ወርቃማ ዕድልን ከግቡ ጋር ተገናኝቶ ቢያገኝም በቀላሉ ኦቮኖን አሳቅፎታል። በመጨረሻም ፋሲሎች ወደ አቻነት ለመምጣት ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።