ሪፖርት | በሁለት አጋማሾች የተቆጠሩ ጎሎች ድሬዳዋን ባለ ድል አድርገዋል

ድሬዳዋ ከተማ በሁለቱ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ጎል ፋሲል ከነማን 2-1 አሸንፏል።

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማ ወልቂጤው ድላቸው ጉዳት ባስተናገዱት እንየው ካሳሁን እና ቢኒያም ጌታቸው ምትክ አሰጋኸኝ ጴጥሮስን እና ዳዊት እስጢፋኖስን ሲተኩ ሽንፈት አስተናግደው የመጡት ፋሲሎች በበኩላቸው በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋች ቅያሪ አስፈልጓቸዋል። በዚህም ታፈሰ ሰለሞንን በሀብታሙ ገዛኸኝ ፣ ዓለምብርሀን ይግዛውን በኦሴ ማውሊ ተክተዋቸዋል።

\"\"

የተመጣጠነ ጨዋታ ባሳየን የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ፋሲሎች አስራ አምስቱን ደቂቃ ያህል የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በመያዝ መሐል ሜዳ መነሻቸውን ካደረጉ የጥቃት ምንጮች ለመንቀሳቀስ ጥረት ሲያደርጉ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው አጀማመራቸው የተቀዛቀዘ መልክ ቢኖረውም በሒደት አጥቂው ቻርለስ ሙሰጊን ባነጣጠረ መልኩ ለመጫወት ጥረት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ወደ ጨዋታው ራሳቸውን መክተት ጀምረዋል። ሱራፌል ዳኛቸው ወደ የላካትን ኳስ ኦሴ ማዊሊ ባለመረጋጋት ከሳታት ጥቃት መልስ በተሻለ ለመጫወት የሞከሩት ድሬዎች አከታትለው ሙከራዎችን አድርገዋል። በጥሩ የቅብብል መንገድ የፋሲል የግብ ክልል ደርሰው ሱራፌል የሰጠውን ዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ጎል መትቶ ሳማኪ ሚካኤል ከያዘበት ሙከራ መልስ ድሬዳዋ ጎል እና መረብን አገናኝተዋል።

\"\"

21ኛው ደቂቃ ላይ አቤል አሰበ ላይ በሳጥኑ ጠርዝ አምሳሉ ጥላሁን የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችን የቅጣት ምት ጋናዊው የግራ መስመር ተከላካይ አብዱላጢፍ መሐመድ በግሩም ሁኔታ ሳማኪ መረብ ላይ አሳርፏታል። ከጎሉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ያለመነቱት ፋሲሎች 24ኛው ደቂቃ ባደረጉት የማጥቃት ሽግግር መናፍ ዐወል ሳጥን ውስጥ በሱራፌል ጌታቸው ጥፋት ተሰርቶበት የተሰጠችን የፍፁም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ቡድኑን ዘደ 1-1 ያሸጋገረች ጎል አድርጓታል።

\"\"

በጎሏ መነቃቃት ውስጥ በይበልጥ የገቡት አፄዎቹ የሱራፌል ዳኛቸው ግልጋሎት በማጠናከር ወደ ቀኝ የድሬዳዋ የሜዳ ክፍል በናትናኤል በኩል አዘንብለው በመጫወት ተጨማሪ ጎልን ለማከል ጥረት አድርገዋል። ሱራፌል ከቅጣት ምት መቶ ዳንኤል በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣበት እና ናትናኤል አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለበት የምትጠቀሰዋ ሙከራ ነች ድሬዳዎች በአንፃሩ ከቅጣት ምት በድጋሚ አብዱለጢፍ ሞክሮ ሳማኪ ካወጣበት ዕድል በኋላ አጋማሹ 1-1 ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ድሬዊች ጨዋታውን ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ መጀመር ቢችሉም የኋላ ኋላ የኃይል ሚዛኑ ወደ ፋሲሎች ያመዘነ ሆኗል። ቡድኑ ተከላካዩ መናፍን ዐወልን በዓለምብርሀን ከተኩ በኋላ ይበልጥ የጥቃት ምንጫቸውን ወደ መስመር አድልተው ዳንኤል ተሾመን የፈተኑ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ታትረዋል። 

\"\"

ከቀኝ የሜዳው ክፍል ናትናኤል ወደ ውስጥ ሰብሮ ገብቶ አክርሮ ሲመታ ዳንኤል ተሾመ ያዳነበት እና 56ኛው ደቂቃ ኦሴ ማዊሊ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያገኛትን ዳንኤል ዳግም የመለሰባቸው የሚጠቀሱት ሙከራዎቻቸው ናቸው። በተጋጣሚያቸው በአመዛኙ ለመበለጥ ቢገደዱም ኳስን ሲያገኙ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚጥሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ ዕድሎችን ሳጥን አካባቢ በመጠጋት ቢያገኙም በአጨራረስ ረገድ ብኩኖች ነበሩ።

\"\"

አቤል አሰበ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በአንድ ሁለት ተቀባብሎ ከርቀት የሞከራትን ሳማኪ ሚካኤል ወደ ውጪ ያወጣበት በአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራቸው ነበረች። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ የፋሲልን የመከላከል ድክመት ተከትሎ በተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩት ድሬዎች 81ኛው ደቂቃ ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሰጌ ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ተከላካዮችን ጭምር በግል ጥረቱ አልፎ ወደ ሳጥን በመግባት ለድሬዳዋ ሁለተኛ ጎልን ከመረብ አሳርፏል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎችን ሳንመለከት ድሬዳዋን ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን 2ለ1 በሆነ ውጤት እንዲያገኝ ሆኗል።

\"\"