ሪፖርት | የጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ወልቂጤን ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ አድርጓል

ወልቂጤ ከተማ ጌታነህ ከበደ በፍፁም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ግቦች ኢትዮጵያ መድንን 2ለ0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ያለበትን ውጤት አሳክቷል።

ሁለቱ ቡድኖች ካለፈው ሳምንት ጨዋታቸው በሦስቱ ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። መድኖች ከሀዋሳው የአቻ ውጤታቸው ጀማል ጣሰው ፣ ማቲያስ ወልደ አረጋይ እና ኤፍሬም ዘካሪያስን በፋሪስ ዕላዊ ፣ ብዙአየው ስይፉ እና አቡበከር ሳኒ ሲተኩ ከድሬዳዋው ሽንፈት አንፃር ወልቂጤ ከተማ ፀጋሰው ድማሙን በቴዎድሮስ በቀለ ፣ አሚር ሙደሲርን በሀብታሙ ሸዋለም ፣ ኪቲካ ጀማን በሐቢብ ከማል የመጀመሪያ ተሰላፊ አድርገው ጀምረዋል።

\"\"

የተቀዛቀዙ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በተበራከተበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሜዳ ላይ ኳስን ቡድኖቹ ከማንሸራሸር በዘለለ ልዩነት ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች እምዛም ነበር። አንፃራዊ በሆነ መልኩ ከተጋጣሚያቸው ሻል ባለ የራስ መተማመን አጋማሹን ለመጫወት የተጉት ወልቂጤዎች ወደ ሦስተኛው የተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረሱ አቀራረባቸው መልካም የሚባል ይመስላል። መድኖች በበኩላቸው ወደ መስመር ዘንበል ብለው ወደ ውስጥ በጥልቀት ለመጫወት ቢሞክሩም ያደርጉት የነበረው የጨዋታ መንገድ ደካማ ይዘትን የተላበሰ ነበር። ጌታነህ ከበደ ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ከርቀት ያደረጋት ጥሩ ሙከራ ወልቂጤን ቀዳሚ ዕድል ፈጣሪዎች አድርጓቸዋል።

መድኖች በሐቢብ ከማል በሀቢብ አማካኝነት በጨዋታ እና ከቆመ ኳስ ወደ ግብ ሞክረው በቀላሉ ወደ ውጪ ከወጣችባቸው ሙከራ ውጪ ጥቃት በመሰንዘሩ ስስታሞች ሆነው ታይተዋል። በተሻለ የራስ መተማመን በመጫወት ከቆሙ ኳሶች በአቡበከር ሳኒ 39ኛው ደቂቃ ላይ በተለይ ቴዎድሮስ ሀሙ ወደ ጎል መቶ ጌታነህ በግንባር ገጭቶ አቡበከር ኑራ በሚገርም ብቃት ከጎልነት ታድጓታል። አጋማሹ ሊጋመስ በጭማሪ ደቂቃ ላይ አወዛጋቢ የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ወልቂጤዎች ግብ አግኝተዋል። 45+1 ላይ ወደ ጎል እየሄደች ያለችን ኳስ አብዱልከሪም መሐመድ በእጅ ነክቷል በሚል የዕለቱ ረዳት ዳኛ ዳንኤል ጥበቡን ዕርዳታ ተጠቅመው ዋና ዳኛው ማኑሄ ወልደፃዲቅ የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት ነው ጌታነህ ከበደ ጎል አድርጓታል። አጋማሹም በወልቂጤ 1ለ0 ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲቀጥል በእንቅስቃሴ ይዘቱ ተመሳሳይ ቅርፅ የነበረውን ለማጥቃት ብዙም ጥረት ማድረግ ያልቻሉበትን የጨዋታ መንገድ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ብናይም የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ በመጠቀሙ ረገድ ወልቂጤ ከተማ የተሻለ መልክ ተላብሰው ታይተዋል። መድኖች ለማጥቃት በዳዱበት የሁለተኛው አጋማሽ አስር ያህል ደቂቃዎች የሐቢብ ከማልን የቀን የሜዳውን ክፍል ተጠቅመው በፈጣን ሽግግር ለመጫወት በሞከሩበት ሒደት ያለቀላቸውን ጥሩ አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም።

\"\"

54ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሐመድ የተስፋዬ መላኩን ስህተት ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ ሐቢብ ከማል ከግቡ ጋር ተገያኝቶ ፋሪስ ዕላዊ ያወጣበት እና ከደቂቃዎች በኋላ ሐቢብ ከቀኝ ወደ ውስጥ አሻግሮ አጥሺዎቹ ሳይጠቀሙ የቀሩበት ተጠቃሽ ዕድሎቻቸው ናቸው። ኳስን በሚይዙበት ወቅት በፍጥነት ከጎል ጋር ለመገናኘት የሚያመነቱት ወልቂጤ ከተማዎች ሁለተኛ ጎላቸውን ወደ ካዝናቸው ከተዋል። 71ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል በረጅሙ የተሻገረን ኳስ ፋሲል አበባየው በግንባር ጨረፎ ያመቻቸለትን ጌታነህ ሳይቸገር ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች መድኖች በብሩክ አማካኝነት ወደ ጨዋታ ልትመልሳቸው የምትችል ግልፅ ዕድል ቢያገኙም ወደ ጎልነት ግቧ መለወጥ ሳትችል ጨዋታው በወልቂጤ 2ለ0 ተቋጭቷል።