የሊጉ የውድድር እና ሥነ ስርዐት ኮሚቴ በሀዋሳ የሚደረጉ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የሰዓት ለውጥ ሲያደርግ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችም ተያይዘው ወጥተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር እና ሥነ ስርዐት ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ቀጣዩ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሀዋሳ ከ12 ሰዓት በኋላ እየጣለ ባለው ሰሞነኛ ከባድ ዝናብ አንፃር የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ በመቸገሩ የሰዓት ለውጥ ማድረጉን ይፋ አድርጓል። የሊጉ አወዳዳሪ አካል 9:00 ሰዓት ይደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች በ7:00 ሰዓት እንዲሁም በ12:00 ሰዓት ይጀምሩ የነበሩ ጨዋታዎች ደግም በ10:00 ሰዓት እንዲደረጉ ነው የሰዓት ለውጥ ውሳኔውን ያስተላለፈው። ከዚህም በተጨማሪ ጨዋታው ተጀምሮ በዝናብ ምክንያት ከተቋረጠ በማግስቱ ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ አርተፊሻል ሜዳ ላይ እንዲጠናቀቅ ወስኗል።
በተያያዘ ዜና ከተላለፉ ቅጣቶች መካከል ጋናዊው የሀዋሳ ግብ ጠባቂ መመመድ ሙንታሪ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ በመውጣቱ 1 ጨዋታ ዕገዳ ፣ ዳግም ንጉሴ ሀዲያ ሆሳዕና በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ካርድ በመመልከቱ 1 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 እንዲከፍል ፣ ረዳት አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ኢትዮጵያ ቡና በ26ኛ ሳምንት በጨዋታ ጊዜ ሆን ብሎ ሰዓት በማባከን ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት በመሆኑ 3 ጨዋታ እንዲታገዱና አስር ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም ወልቂጤ ከተማ እና ሃዋሳ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለባቸው ከአምስት በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቦቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡