የተቀዛቀዘ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተበራከተበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለገጣፎ ለገዳዲን 2ለ1 በመርታት የሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን ከረታበት ስብስቡ ቅጣት ባስተናገዱት ፍሪምፓንግ ሜንሱ እና ረመዳን የሱፍ ምትክ ምኞች ደበበ እና ሱለይማን ሀሚድን ሲጠቀሙ ከአዳማው ድል አንፃር ለገጣፎ ለገዳዲዎች ታምራት አየለን በበረከት ተሰማ የተኩበት ብቸኛ ለወሰጣቸው ሆኗል።
አሰልቺ የሜዳ ላይ ቆይታ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ያልተረጋጉ ቅብብሎች ተበራክተው የታየበትን ሒደት አስተውለናል። የጨዋታው ደቂቃ ሲገፋ ወደ መስመር በማድላት ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ፈረሰኞቹ 16ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት የመጀመሪያ አጋጣሚ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። ከወትሮ የመስመር ተሰላፊነቱ ወደ መሐል እንዲጫወት የተደረገው ቢኒያም በላይ ከቀኝ የለገጣፎ የሜዳ ክፍል ወደ ግብ ክልል ያሻማውን ኳስ ከተከላካዮች መሐል ዘሎ በመነሳት ልማደኛው አጥቂ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባር ኮፊ ሜንሳህ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ተስፋዬ ነጋሽን በጥልቀት ተስቦ እንዲጫወት በማድረግ ተሻጋሪ የግንባር ኳሶችን ለኢብሳ ለመላክ ጥረቶች ያደርጉ የነበሩት ለገጣፎዎች ተስፋዬ አከታትሎ ከርቀት ባደረጋቸው ሙከራዎች ተጋጣሚን መፈተን ችለዋል። ጨዋታው ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ቡድኖች በቀሩት ደቂቃ መንቀሳቀስ ቢችሉም ቀዝቃዛነቱ እና ሳቢነቱ ቀንሶ ይታይ የነበረው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 መሪነት ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሱራፌል እና ካርሎስን ወደ ሜዳ በማስገባት ወደ ጨዋታ ቅኝት ራሳቸውን ለመክተት መንቀሳቀስ ቢችሉም በቀላሉ ግን የሚያገኟቸውን ዕድሎች መጠቀም ላይ ደካሞች ናቸው። በአንፃሩ ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን መርጠው ነገር ግን ኳስን በሚያገኙበት ወቅት ለአጥቂዎቻቸው በማሻገር ለመጫወት ያቀዱት ፈረሰኞቹ ሔኖክ ወደ ውስጥ አሻምቶ ቸርነት በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ታካ ኳሷ ከወጣች ከጥቂት ደቂቃዎች መልስ ሁለተኛ ግባቸውን ወደ ካዝናቸው ከተዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር ካስጀመረው ጥቃት መነሻነት ሀይደር ከቢኒያም ጋር በመቀባበል በግሩም ሁኔታ አልፎ በግብ ጠባቂው አናት ላይ ማስቆጠር ችሏል።
ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ በተሻለ መነቃቃት ውስጥ እየገቡ የመጡት ለገጣፎዎች በካርሎስ እና ኦካይ አማካኝነት ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎችን ግብ ለማግኘት ቢታትሩም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ደካማ ከመሆኑ አንፃር በቀላሉ ዕድላቸው ሲከሽፍ ነበር። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ዳግማዊ ዐርአያን ተጠቅመው በይበልጥ የቀኝ መስመሩን ለመጠቀም ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥቂት ጥረቶችን አድርገዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዐወል ከማዕዘን ሲያሻማ ባህሩ ነጋሽ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በቀላሉ መረብ ላይ አሳርፏት። በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ1 ተጠናቋል። ፈረሰኞቹም በስምንት ነጥብ ልዩነት መሪነታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።