በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና
ቀን 7 ሰዓት ላይ ተቃራኒ የጨዋታ ሳምንት ባሳለፉ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በወልቂጤ ከተማ የውድድሩን ሰባተኛ ሽንፈት ያስተናገዱት መድኖች ሁሉ ነገራቸውን ባጡበት ጨዋታ ካለፉት 14 ጨዋታዎች ለ3ኛ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ የወጡበት ነበር። በሜዳሊያው ደረጃ መቆየት ያን ያህል የሚያሰጋቸው ባይሆንም በቀጣይ ዓመት የአህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የባህርዳር ከተማን ውጤት መጠበቅ ግድ ቢላቸውም ሁሉንም ጨዋታዎች ድል በማድረግ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል። ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግዱ መውጣታቸው ጥሩ ጎናቸው የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ግን አራት ግቦችን አስተናግደው ከሲዳማ ቡና እና ከወልቂጤ ከተማ ዕኩል በውድድር ዓመቱ አራተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (36) እንዲመዘገብባቸው አስገድዷቸዋል። ዋና አሰልጣኙ ለ 90 ደቂቃ ያህል ቡድናቸው ጋር መገኘት አለመቻላቸውን ተከትሎ ቡድኑን ሜዳ ላይ የመምራት ዕድል ያገኙት ምክትል አሰልጣኙ ለይኩን ታደሰ በመሯቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ድል ፣ አቻ እና ሽንፈት አድናቆት አስችሯቸው የነበረውን ጨዋታ አንብቦ የመቀየር ሂደት ጥያቄ ውስጥ እንዳይከትባቸው የነገውን ድል አብዝተው ይፈልጉታል።
ከሜዳሊያው ደረጃ በ 7 ነጥቦች ርቀት ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የነገውን ጨዋታ አሸንፈው ልዩነቱን ወደ 4 በማጥበብ በከፍተኛ መሻሻል ላይ ያለውን እንቅስቃሴያቸውን በቁጥር ለመደገፍ ጥረት ያደርጋሉ። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች የተጋጣሚን መረብ መድፈር የቻሉት ቡናዎች በስድስቱ መረባቸውን ማስደፈራቸው ሊያሳስባቸው የሚችለው ብቸኛው ነገር ነው። በተለይም ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ መድን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ዕኩል ከፍተኛውን የግብ መጠን (48) ማስቆጠሩ የኋላ መስመራቸው ላይ ሥራ ሊያበዛባቸው እንደሚችል ይጠቁማል። ከባህርዳሩ ቆይታው በኋላ አንድም ተከታታይ ድል ያላስመዘገበው ቡድኑ የሀዋሳ ከተማ ቆይታውን ይህን ድል አሳክቶ ለማጠናቀቅ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በሚቋረጥበት ወቅት በቂ የዕረፍት ጊዜ (21 ቀናት) የሚያገኝ በመሆኑ ለአዳማ ቆይታው መልካም ዜና እንደሚሆንለትም ይገመታል።
የኢትዮጵያ መድን ሙሉ ስብስብ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ሬድዋን ናስር ብቻ በጉዳት የማይኖር ተጫዋች ነው።
ሁለቱ ቡድኖች 26 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 11 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መድን 6 ጊዜ አሸንፏል ፤ 9 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና 42 ጎሎች ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ 29 ጎሎች በስሙ አሉት።
ወልቂጤ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
ላለመውረድ እና የሜዳሊያ ደረጃ ውስጥ ሆኖ ለመጨረስ የሚደረገው ተጠባቂ ፍልሚያ ቀን 10 ሰዓት ሲል ይጀምራል።
ከወራጅ ቀጠናው ሁለት ነጥቦችን ብቻ ርቀው የተቀመጡት ሠራተኞቹ በድሬዳዋ ከተሸነፉ በኋላ በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ኢትዮጵያ መድን ላይ የ2-0 ወሳኝ ድል ቢቀዳጁም ያሉበት ደረጃ ዕረፍትን የሚሰጥ አይደለም። ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች እየተፈተኑ ያላቸውን ሁሉ እየሰጡ እዚህ የደረሱት ሠራተኞች በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ጨዋታ ላይ ብቻ ያሳኩትን ተከታታይ ድል በነገው ዕለትም አሳክቶ ከወራጅ ቀጠናው ለመሸሽ ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድናቸው ሜዳ ውስጥ የሚያሳየው ብቃት ለመውረድ እንደማያበቃው ቢናገሩም ከጌታነህ ውጪ ያሉ እንደነ አቤል ነጋሽ ያሉ አጥቂዎች ብቃቱ ቢኖራቸውም በልምድ ማነስ ግቦችን እያስቆጠሩ አለመሆኑ ማሳካት ለሚፈልጉት ዕቅድ መጠነኛ መሰናክል እንደሚሆንባቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ሲጠቁሙ ቁጥሮችም ሀሳባቸውን ይደግፉላቸዋል።
እንደ 9ኛው እና 10ኛው ሳምንት ተከታታይ ሽንፈት ባለፈው ሳምንትም ያስተናገዱት አፄዎቹ አሁንም ቢሆን ወጥ የሆነ ብቃት ማሳየት ተስኗቸው ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ በአንድ ነጥብ ልዩነት እንዲቀመጡ አስገድዷቸዋል። በሱራፌል ዳኛቸው በሚመራው የአማካይ ስፈራ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል በመጠኑ የተሳካ ጊዜን የሚያሳልፈው ቡድኑ በአማካይ በአንድ ጨዋታ (1.03) ግብ ብቻ የሚያስቆጥረው ደካማ የአጥቂ መስመራቸው ድል እንዳያደርግ ማነቆ ሆኖበታል። የነገው ተጋጣሚያቸው ላለመውረድ ከመጫወቱ እና የሊጉን ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ጌታነህ ከበደን መያዙ ደግሞ ሁለቱም ሳጥን ውስጥ ሥራ ሊበዛባቸው እንደሚችል ይጠቁማል።
በወልቂጤ ከተማ በኩል አዳነ በላይነህ እና አፈወርቅ ኃይሉ በጉዳት እንዲሁም ዋሃቡ አዳምስ በቅጣት የማይኖሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ በፋሲል ከነማ በከል በዛብህ መለዩ በጉዳት ምክንያት ከውድድር ዓመቱ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ ታፈሠ ሰለሞንም በዲስፕሊን ምክንያት ዕግድ እንደተላለፈበት ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሦስቱን ጨዋታ በተመሳሳይ 1-0 ማሸነፍ ሲችል ወልቂጤ ከተማ አምና አንድ ጊዜ 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል። የዘንድሮው ግንኙነታቸው ያለ ግብ መጠናቀቁ ይታወሳል።