\”ሥራው የተበላሸው የመጀመሪያው ምልመላ ላይ ነው።\” – አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ
\”በቀጣይ አዳማ ላይ ለሚኖረን ቆይታ ይህ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል።\” – አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ
አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ስለ ጨዋታው…
\”እንቅስቃሴው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ ነበር። መጀመሪያ ግብ አስቆጠሩብን የገባው ጎልም አላስፈላጊ ነው ፤ ጥፋት ተሠርቶ ነበር። ከዛ በኋላ አስቆጠርን። በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር።\”
ማጥቃቱ ላይ ስለመዳከማቸው…
\”በፊትም ቢሆን አጥቂዎቻችን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ደካማ ነበር። ግን ያው ባለው ሰው ነው የምትንቀሳቀሰው እና በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ያሉብንን ክፍተቶች አስተካክለን ለመምጣት እንሞክራለን።\”
ቡድኑ ከድል ስለራቀበት ምክንያት…
\”ሥራው የተበላሸው የመጀመሪያው ምልመላ ላይ ነው። ያኔ ጥሩ ነገር ተሠርቶ ቢሆን ቡድናችን እዚህ ላይ አይገኝም ነበር። ያንን ደግሞ ወደፊት ወጣቶች ላይ ተሠርቶ እንደገና ራሱን አሻሽሎ የሚመጣበት መንገድ ይፈጠራል።\”
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለ ጨዋታው…
\”የዛሬው ጨዋታ ለኛ ከባድ ነው ፤ ለነሱ ያን ያህል ልዩነት የማያመጣ ቢሆንም። ለኛ ግን እጅግ በጣም አስጨናቂ እና አስቸጋሪ የነበረበት ምክንያት ሁሉም ቡድኖች ተሰብስበን ያለነው አንድ ቦታ ላይ ነው። ከዛ ቦታ ለመውጣት እና ደረጃችንን ከፍ አድርገን በቀጣይ አዳማ ላይ ለሚኖረን ቆይታ ይህ ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆነናል እና ውጥረት የነበረብንም ለዛ ነው።\”
በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ስላስቆጠረው ባዬ ገዛኸኝ…
\”ባዬ ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ጎበዝ አጥቂዎች አንዱ ነው። ይህ ለባዬ አዲስ አይደለም። በተለያየ ጊዜ በካርድ እና በጉዳት ማረፉ ጎዳን እንጂ ብዙ ጎሎችን ማግኘት እንችል ነበር እሱ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎልን ቢሆን ኖሮ።\”
ተከላካይ መስመር ላይ ስለታየው የወጥነት ችግር…
\”ትክክል ነው። መሃል ተከላካይ ቦታ ላይ ዳግም በአምስት ቢጫ ፍሬዘር ደግሞ በቀይ ካርድ አርፈውብናል። ያንን ቦታ የሚተኩ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የሉም። ስለዚህ ቃለአብም ወጣት ነው በዚህ ዓመት ብዙ ጨዋታዎችን አላደረገም። ሄኖክ የግራ መስመር ተከላካይ ነው ፤ ገና ወደዛ ቦታ እየመጣ ያለ ልጅ ነው። ስለዚህ በእነዚህ ሁለት ልምድ የጎደላቸው ተጫዋቾች ይህን ውጤት ይዞ መውጣት ለኛ ትልቅ ነው።\”